ከአስረኛው ሳምንት ጨዋታዎች መካከል አንዱ የሆነው የድቻ እና ወልዋሎ ጨዋታን የተመለከተው ዳሰሳችንን እንደሚከተለው እናስነብባችኋለን።
በሊጉ የመጨረሻ ድላቸውን ካስመዘገቡ ሦስት ጨዋታዎች ያለፏቸው ወላይታ ድቻ እና ወልዋሎ ዓ/ዩ ነገ 09፡00 ላይ በሶዶ ስታድየም ይገናኛሉ። በደደቢት ያልተጠቀ ሽንፈት የገጠማቸው ወላይታ ድቻዎች አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ሲኖራቸው እስካሁን ሁለት ድል ብቻ ነው ማስመዝገብ የቻሉት። ከሰንጠረዡ አጋማሽ በመንሸራተትም አሁን 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በተመሳሳይ የአቋም መዋዠቅ የሚታይበት ወልዋሎም ሰባተኛ ደረጃን ይያዝ እንጂ ደደቢትን ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ በሦስት ጨዋታዎች ግብ አላስቆጠረም። ሁለቱ ቡድኖች ወጣ ገባ የሆነው አቋማቸውን ለማስተካከልም የነገውን ጨዋታ በአሸናፊነት ማጠናቀቅ ይጠበቅባቸዋል። ያን ማድረግ ከቻሉ ድቻ ወደ ደረጃ ሰንጠረዡ አጋማሽ ወልዋሎ ደግሞ ወደ መሪዎቹ የመቅረብ ዕድል ይኖራቸዋል።
በጨዋታው ወላይታ ድቻ እርቂሁን ተስፋዬን ከጉዳት መልስ ሲያገኝ በፌድሬሽኑ የአራት ጨዋታዎች ቅጣት የተጣለበትን እሸቱ መናን በቅጣት ኃይማኖት ወርቁ እና ሄኖክ ኢሳያስን ደግሞ በጉዳት እንዲሁም ሙባረክ ሽኩርን በህመም ምክንያት የማይጠቀም የሆናል። በወልዋሎ በኩል ዳንኤል አድሓኖም ፣ ዋለልኝ ገብሬ እና ኤፍሬም ኃይለማርያም በጉዳት እንደማይሰለፉ ሲታወቅ የብርሃኑ ቦጋለ ፣ አፈወርቅ ኃይሉ እና ሬችሞንድ አዶንጎ መግባትም አጠራጣሪ ሆኗል። ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ አስራት መገርሳን በቅጣት ምክንያት ያጣል።
የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– ወልዋሎ ዓ/ዩ ሊጉን በተቀላቀለበት የአምናው የውድድር ዓመት የተገናኙባቸው ሁለቱም ጨዋታዎች በ 1-1 ውጤት የተጠናቀቁ ነበሩ።
– ወላይታድ ድቻ ሜዳው ላይ ካደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች ሁለቱን በ1-0 ውጤት ሲያሸንፍ በመጨረሻው ጨዋታ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር 1-1 ተለያይቷል።
– ወልዋሎ ዓ/ዩ አራት ጨዋታዎችን ከመቐለ ውጪ ያደረገ ሲሆን ሁለቱን ተሸንፎ አንዴ አቻ ሲወጣ አንድ ጊዜ ደግሞ ድል ቀንቶታል። ግብ ማስቆጠር የቻለውም መከላከያን 1-0 ባሸነፈበት ጨዋታ ብቻ ነው።
ዳኛ
– ሣምንት በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውን የወልዋሎ እና ፋሲልን ጨዋታ የዳኘው ወልዴ ንዳው በዚህም ሳምንት ይህንን ጨዋታ ለመምራት ተመድቧል። ወልዴ እስካሁን በሦስት ጨዋታዎች አስር የማስጠንቀቂያ ካርዶችን መዟል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ወላይታ ድቻ (4-1-4-1)
ታሪክ ጌትነት
ተክሉ ታፈሰ – ዐወል አብደላ – ውብሸት ዓለማየሁ – ያሬድ ዳዊት
በረከት ወልዴ
ቸርነት ጉግሳ – አብዱልሰመድ ዓሊ – ፍፁም ተፈሪ – እዮብ ዓለማየሁ
አንዱዓለም ንጉሴ
ወልዋሎ ዓ.ዩ (4-3-3)
አብዱልዓዚዝ ኬይታ
እንየው ካሳሁን – ደስታ ደሙ – ቢኒያም ሲራጅ – ብርሀኑ ቦጋለ
አማኑኤል ጎበና – ብርሀኑ አሻሞ – አፈወርቅ ኃይሉ
ፕሪንስ ሰቨሪንሆ – ሪችሞንድ ኦዶንጎ – ኤፍሬም አሻሞ