ሴቶች አንደኛ ዲቪዝዮን | ቅዱስ ጊዮርጊስ የዓመቱን ሁለተኛ ድል አስመዝግቧል

በስምንተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የዛሬ ብቸኛ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮ ኤሌትሪክን 3-0 በመርታት ከተከታታይ ሽንፈት ወደ አሸናፊነት ተመልሷል።

08:00 በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው እና ሁለቱም ቡድኖች በተከታታይ ጨዋታ ከደረሰባቸው ሽንፈት ለማገገም ይጠቀሙበታል ተብሎ በተጠበቀው በዚህ ጨዋታ በእንቅስቃሴ ተሽለው የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ምንም እንኳን የመጀመርያ ጎላቸውን እስኪያስቆጥሩ ድረስ የኢትዮ ኤሌትሪክን ተከለካዮች በማለፍ ጠንካራ የጎል ሙከራ መፍጠር ቢቸገሩም ከቆሙ ኳሶች የሚፈጥሩት አደጋ ተሳክቶላቸው 28ኛው ደቂቃ ዳግማዊት ሰለሞን ከማዕዘን የተሻገረ ኳስን በግንባሯ በመግጨት ቅዱስ ጊዮርጊስን ቀዳሚ ማድረግ ችላለች። 


የእየሩሳሌም ነጋሽ ቡድን ኢትዮ ኤሌትሪክ መሀል ሜዳ ላይ የተገደበ እንቅስቃሴ ብቻ አተኩረው ወደ ፊት የማይሄድ አጨዋወት ዋጋ ሲያስከፍላቸው አጥቂዋ ዓለምነሸ ገረምው በግሏ የምታደርገው ጥረት ካልሆነ በስተቀር የጎል ዕድል መፍጠር አልቻሉም ነበር። ጎሉን ካስቆጠሩ በኋላ ጊዮርጊሶች በደጋፊዎቻቸው ታጅበው ብልጫ የወሰዱ ሲሆን  በ39ኛው ደቂቃ በጥሩ ቅብብል ወደ ጎል ደርሰው ግራ መስመር ላይ አጥቂዋ ፋና ዘነበ በግራ እግሯ አክርራ ብትመታውም የግቡን ቋሚ ታኮ ለጥቂት ሊወጣባት ችሏል። በድጋሚ ከጥቂት ደቂቃ በኋላ 45ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ ቦታ ፋነ ዘነበ ያገኘችውን ኳስ በጥሩ ሁኔታ ወደ ጎል ብትመታውም የግቡ ቋሚ ቢመልስባትም ራሷ ደግማ ኳሱን አግኝታ ወደ ጎልነት በመቀየር የፈረሰኞቹን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጋ በ2-0 መሪነት እረፍት እንዲወጡ አድርጋለች።


በሁለተኛው አጋማሽ ብልጫ ወስደው የቀጠሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሚገርም ሁኔታ ከሳጥን ውጭ ኳሱን በደረቷ አብረዳ በ57 ኛው ደቂቃ ብርሃን ኃይለሦላሴ ባስቆጠረችው ግሩም ጎል መሪነታቸውን ወደ ሦስት ከፍ አድርገዋል። ከእረፍት መልስ ምንም የእንቅስቃሴ ለውጥ ማድረግ ያልቻሉት ኢትዮ ኤሌትሪኮች አልፎ አልፎ ከሚያደርጉት ወደ ጎል ለመቅረብ ጥረት  በዘለለ የረባ እንቅስቃሴ ማድረግ አቅቷቸው ተዳክመው ነበር የቀረቡት። 67ኛው ደቂቃ ዓለምነሽ ገረመው በጠንካራ ምት ሞክራ ግብ ጠባቂዋ ያዳነችው እንዲሁም ተቀይራ በመግባት ከቅጣት ምት የጎል እድል መፍጠር የምትታወቀው የመስመር አጥቂዋ መሳይ ተመስገን በሦስት አጋጣሚ  የግቡ አግዳሚ የመለሰባት የሚያስቆጭ አጋጣሚዎች ነበሩ። ጨዋታው በተደጋጋሚ በተለያዩ ምክንያቶች እየተቆራረጠ ቀጥሎ በሁለቱም በኩል ሌሎች ተጨማሪ ጎሎች ሳንመለከት በበርካታ ደጋፊዎች መሀል በተጫወቱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች የበላይነት 3-0 ማሸነፍ ተጠናቋል።



Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *