ሪፖርት | ሲዳማ ቡና እና ኢትዮጵያ ቡና ነጥብ ተጋርተዋል

ሲዳማ ቡና ኢትዮጵያ ቡናን ባስተናገደበት የዛሬው የ10ኛ ሳምንት ጨዋታ በአቡብከር ነስሩ ጎል ሲመራ ቢቆይም መሀመድ ናስር ከተጠባባቂ ወንበር በመነሳት ታድጎታል።

ሲዳማ ቡና መቐለ ላይ የዓመቱ የመጀመሪያ ሽንፈት ሲደርስበት ከተጠቀመበት የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ አድርጓል። በዚህም ሚሊዮን ሰለሞን ፣ አበባየሁ ዮሃንስ ወንድሜነህ ዓይናለም እና ፀጋዬ ባልቻን በማስቀመጥ በምትካቸው ሰንደይ ሙቱኩ ፣ ግሩም አሰፋ ፣ ዳዊት ተፈራ እና ተመስገን ገብረፃዲቅን ተጠቅሟል። ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ስሑል ሽረን ከረታበት ጨዋታ የጋብቻ ስነ ስርዓቱን እያከናወነ የሚገኘው ተካልኝ ደጀኔን እና ዳንኤል ደምሴን በእያሱ ታምሩ እና ሳምሶን ጥላሀን በመተካት ጨዋታውን ጀምሯል።

ቁጥሩ እጅግ በርካታ በሆነ ተመልካች ፊት የተጀመረው ጨዋታ እንደ ስታድየሙ ሁሉ ሜዳ ላይም ሞቅ ያል ስሜት ይዞ ነበር። ቢሆንም ከታየው ጠንካራ ፉክክር በተቃራኒ የመጀመሪያው አጋማሽ ጥቂት የግብ ሙከራዎች ብቻ የተደረጉበት ነበር። አራተኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ረሺድ ወደፊት በላከው ኳስ አቡበከር ነስሩ ሳጥን ውስጥ ቢገባም በግብ ጠባቂው ፍቅሩ ወዴሳ የተቀደመበት አጋጣሚም የጨዋታው የመጀመሪያ አደገኛ እንቅስቃሴ ነበር። የሲዳማን የመስመር አጥቂዎች በመቆጣጠር ላይ ትኩረት ያደረጉት የኢትዮጵያ ቡና መስመር ተመላላሾች የማጥቃት ተሳትፎ አናሳ የነበረ በመሆኑ ቡድኑ በሲዳማ ሜዳ ላይ በቁጥር እየተበለጠ ለብቸኛው አጥቂ ሱለይማን ሎክዋ ዕድሎችን ለመፍጠር አቅም ሲያጣ ተስተውሏል። 7ኛው ደቂቃ ላይ ሎክዋ በግራ መስመር ገብቶ የሞከረው እና በሲዳማ ተከላካዮች ተጨርፎ ለጥቂት የወጣው ኳስ ግን ለግብ የቀረበ ነበር።

 

በሂደት ጫናቸው እየጎላ የመጣው ሲዳማዎችም ለረጅም ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ቡና ሙሉ ለሙሉ ሜዳው ላይ እንዲቆይ ማድረግ ቢችሉም ከኋላ ያሉትን አምስት ተከላካዮች ሰብረው መግባት ግን አልተቻላቸውም። የቡድኑ ዋነኛ የጥቃት መሳሪያዎች የሆኑት የመስመር አጥቂዎች ከተጋጣሚ ጀርባ የሚፈልጉትን ክፍተት ማግኘት ባለመቻላቸው አደገኝነታቸው ቀንሶ ነበር። አማካይ ክፍል ላይ ብቸኛው የቡድኑ የፈጠራ ምንጭ የነበረው ዳዊት ተፈራ ጥሩ ቢንቀሳቀስም ከሳምሶን ጥላሁን እና ካሉሻ አልሀሰን ጋር ፊት ለፊት የመጋፈጥ ግዴታ ውስጥ የሚገባባቸው ጊዜያት በርካታ ነበሩ። በመሆኑም ሲዳማ ብልጫ በወሰደባቸው ደቂቃዎች ያደረጋቸው ቅብብሎች አብዛኞቹ የጎንዮሽ ነበሩ። 17ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ገዛኸኝ ከቀኝ መስመር አሳልፎለት ተመስገን ከግቡ አፋፍ ላይ ሲሞክር ተከላካዮች ያወጡበት እና 26ኛው ደቂቃ ላይ ግርማ በቀለ ከርቀት ያደረገው ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራም በሲዳማ በኩል ብቸኛ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።

በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ራሳቸውን ከተፈጠረባቸው ጫና አላቀው ወደ ፊት መጠጋት የቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች አንድ አደገኛ ሙከራ አድርገዋል። ሚኪያስ በግራ በኩል ከተከላካዮች ጀርባ ለገባው አቡበከር በግሩም ሁኔታ ያደረሰው ኳስ በአቡበከር ተሞክሮ ለጥቂት ነበር በግቡ ቋሚ በኩል የወጣው። ከዚህ ሙከራ በኋላ የነበረው የቡድኖቹ እንቅስቃሴ ግን እየተቃዛቀዘ የሄደ ነበር።

ከእረፍት መልስ ሶስት ደቂቃዎች እንደተቆጠሩ ኢትዮጵያ ቡና ግብ ማስቆጠር ችሏል። በግራ መስመር ከአልሀሰን ካሉሻ የተጨረፈን ኳስ ሎክዋ ለአቡበከር አድርሶት አቡበከር አጋጣሚውን በተረጋጋ አጨራረስ ወደ ግብነት ለውጦታል። በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ግን የአዲስ ግደይ የጨዋታ ውጪ ጎል ፣ የሲዳማ ፍፁም ቅጣት ምት ይገባኛል ጥያቄ እና ሎክዋ ተጎድቶ በሚወጣበት ወቅት የተነሳው ግርግር ጨዋታው እስከመጨረሻው ድረስ ውጥረት በተሞላበት መንገድ እንዲቀጥል ያደረጉ ክስተቶች ነበሩ። የዳንኤል ደምሴን መግባት ትከትሎ መሀል ላይ ጉልበት ያገኙት ኢትዮጵያ ቡናዎች እስከ 65ኛው ደቂቃ ድረስ አማካይ ክፍል ላይ ኳሶችን በማስጣል በፍጥነት በተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ የመግባት አዝማሚያ ይታይባቸው ነበር። ሆኖም ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር በጥልቀት ወደኋላ ተስበው እና ሁለቱን መስመሮች ዘግተው በመከላከል ውጤቱን ማስጠበቅ ላይ ትኩረት አድርገዋል።

የተጋጣሚያቸው ወደ ኋላ የተሳበ አቀራረብ ምክንያት ክፍተት ማግኘት የተቸገሩት ሲዳማዎች ወደ ተሻጋሪ ኳሶች ለማዘንበል ተገደዋል። መሀመድ ናስርን ቀይረው በማስገባትም የአጥቂዎቻቸውን ቁጥር ጨምረው ይበልጥ ለተሻጋሪ ኳሶች ራሳቸን አዘጋጅተው ማጥቃታቸውን ሲቀጥሉ ከ80ኛው ደቂቃ በኋላ ቡና አልፎ አልፎ ለማጥቃት በሚያደርገው ጥረት ውስጥ የተከላካይ መስመሩ ወደ መሀል ሜዳው የተጠጋባቸውን ክፍተቶች ማግኘት ጀምረዋል። በዚህም 80ኛው ደቂቃ ላይ በሀብታሙ አማካይነት ጥሩ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ አግኝተው በልተመጠነ ቅብብል ሲመክንባቸው 83ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ከቆመ ኳስ በተገኘ ዕድል የኢትዮጵያ ኑና ግብ አፋፍ ላይ በርካታ ተጫዋቾች የተራኮቱበት የግብ ዕድል ለጥቂት ወጥቶባቸዋል። ነገር ግን ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር በቡና ሳጥን ውስጥ የተገኙበት አጋጣሚ ወደ ግብነት ተቀይሯል። ተቀይሮ የገባው አዲሱ ተስፋዬ የመታው ኳስ በቡና ተከላካዮች ሲጨረፍ ሌላው ተቀያሪ መሀመድ ናስር አግኝቶ ሲዳማን ነጥብ እንዲጋራ ያስቻለች ግብ አስቆጥሯል። በቀሩት ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች በተለይም ሲዳማዎች ወደ ግብ ለመድረስ ሲጣደፉ ቢታይም ጨዋታው ሌላ ግብ ሳይስተናገድበት 1-1 ተጠናቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *