ሀዋሳ ላይ የተደረገው የሲዳማ ቡና እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች በጨዋታው ዙሪያ እንዲህ ብለዋል።
” ተጫዋቾቼ ዛሬ ባሳዩት መነሳሳት በጣሙን ኮርቼባቸዋልው” ዲዲዬ ጎሜስ – ኢትዮጵያ ቡና
“ጨዋታው ጥሩ ነበር። የሲዳማ ቡናን የማጥቂያ ጠንካራ ጎኖች ለመቆጣጠር ሞክረናል። ሲያጠቁ መሀል ላይ በተለይም በግራ በኩል ከኋላ ሰፊ ክፈተት ይተው የነበረ በመሆኑም ያንን ለመጠቀም ጥረናል። ግብም አስቆጥረናል። ነገር ግን መጨረሻ ላይ ውጤቱ ከዛም በላይ ከፍ እንዲል ያደረግነው እንቅስቃሴ ዋጋ አስከፍሎናል። በጥቅሉ ግን እዚህ መጥተው የተሸነፉ ብዙ ቡድኖች እንደመኖራቸው ውጤቱ ጥሩ ነው። አሁንም አንደኛ መሆናችንም መልካም ነው። ያለፈው ሳምንት በጣም ከባድ ነበር። ተጫዋቾቼ ዛሬ ባሳዩት መነሳሳት በጣሙን ኮርቼባቸዋለው ፤ አምንባቸዋለው እነሱም ያምኑብኛል። የክለቡ ፕሬዘደንትም በኔ ላይ ላሳዩት ዕምነትም ማመስገን ፈልጋለው።”
አሰልጣኙ በተለይም ቡድኑ ወደ መከላከል ሲሸጋገር ይታይባቸው ስለነበረው ብስጭት
” ስህተቶችን እየሰራን ስለነበር ነው። በጣም ጀብደኛ ሆነን ተጭነን ለማጥቃት የጣርንባቸው ደቂቃዎች ነበሩ። በዛን ወቅት ለነሱ ለማጥቃት የሚመች ክፍተት ስንሰጣቸው ነበር። ለዛም ነበር በመጠኑ ስበሰጭ የነበረው። ”
” ለማስከፈት ተቸግረን ነበር ” ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና
“ጨዋታው ጥሩ ነበር። በእንቅስቃሴ በሁለቱም አጋማሾች ኳስ ተቆጣጥረን ለመጫወት ሞክረናል። ተጋጣሚያችን ከጠበቅነው በላይ ወደ ኋላ ሸሽቶ ሲጫወት ነበር ፤ እኔ ቡናን እንደዚህ አላውቀውም። ዞሮ ዞሮ የአጥቂዎችን ቁጥር ጨምረን ለማስከፈት ሞክረናል። ለማስከፈት ተቸግረን ነበር ፤ በዛም መሀል ነበር ግብ ያስቆጠሩብን። ነገር ግን ባደረግናቸው ቅያሪዎች አቻ መውጣት ችለናል። ከዛ ውጪ ግን የተሻረብን ጎል መፅደቅ ነበረበት ፍፁም ቅጣት ምትም ይገባን ነበር። ዳኝነቱ ለኔ አላሳመነኝም።”