ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ፋሲል ከነማ ከ ደደቢት

ዛሬ ጎንደር ላይ በሚደረገው ብቸኛ የተስተካካይ መርሀ ግብር ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

የስምንተኛ ሳምንት መርሀ ግብር የነበረው ይህ ጨዋታ በአማራ እና ትግራይ ክለቦች መካከል ሳይደረጉ ከቀሩ ጨዋታዋች መካከል የመጨረሻው ነበር። ምንም እንኳን በቅድሚያ ነገ እንዲደረግ ቀን ተቆርጦለት የነበረ ቢሆንም ፋሲል ከነማ ወላይታ ድቻን የሚያስተናግድበት የቅዳሜው ጨዋታ በጥምቀት በዓል አከባበር ምክንያት ወደ አርብ በመምጣቱ ነው ዛሬ ላይ የሚከናወነው።

 በ12 ነጥቦች ዘጠነኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ፋሲል ሊጉን በሽንፈት ቢጀምርም በቀጣዮቹ ጨዋታዎች መልካም የሚባል ጉዞ ማድረግ ችሏል። የዛሬውን ጨምሮ ሦስት ተስተካካይ ጨዋታዎች ያለው በመሆኑም ሊጉን እስከመምራት የሚያደርሰው ዕድል እጁ ላይ ይገኛል። በዘጠነኛው ሳምንት ወላይታ ድቻን በማሸነፍ የመጀመሪያ ድሉን አሳክቶ የነበረው ደደቢት ግን በባህርዳር በደረሰበት ሽንፈት ውጤቱን ማስቀጠል ሳይችል በሊጉ ግርጌ እንደተቀመጠ ይገኛል። ከዚህ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት ከቻለ ግን ቢያንስ ሁለት ደረጃዎችን ማሻሻል ይችላል። 

በጨዋታው ፋሲል ከነማ የመስመር አጥቂው ሽመክት ጉግሳን በአምስተኛ ቢጫ ካርድ ምክንያት የማይጠቀም ሲሆን ፋሲል አስማማውም ከጉዳቱ አላገገመም። በደደቢት በኩል ግን ምንም የቅጣትም ሆነ የጉዳት ዜና ያልተሰማ በመሆኑ በባህር ዳሩ ጨዋታ የተጠቀመውን ስብስብ በመያዝ ወደ ጎንደር ተሻግሯል።

ጨዋታው ባለሜዳዎቹ ፋሲል ከነማዎች ኳስን ተቆጣጥረው በመጫወት አብዛኛውን ደቂቃዎች በደደቢት የሜዳ ክፍል ላይ ሊቆዩ ይሚችሉበት እና ደደቢት ደግሞ ጥንቃቄ የተሞላበት አቀራረብን ይዞ እንደሚገባ የሚጠበቅበት ነው። በመሆኑም ለፋሲል ከነማዎች በአምስቱ የአማካይ መስመር ተሰላፊዎቹ ድጋፍ ሊያገኝ የሚችለው የደደቢትን የመከላከል አደረጃጀት ማለፈ ዋናው ፈተና ሲሆን ቡድኑ ቀጥተኛ ኳሶችን ወደ መስመር አጥቂዎቹ ማሳለፈን እንዲሁም ከቆሙ ኳሶች የሚገኙ ዕድሎችን ለመጠቀም የሚያደርገው ጥረት ይጠበቃል። በደደቢት በኩል የፋሲልን የማጥቃት ፍላጎት ተከትሎ ከኋላ የሚፈጠሩ ክፍተቶችን በፈጣን ሽግግር የመጠቀም ዕቅድ እንደሚኖረው ይገመታል። በዚህም ወደ ፊት በቀጥታ የሚላኩ ኳሶች ወሳኝ ሲሆኑ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው የቡድኑ አማካዮችም አጋጣሚዎቹ በሚፈጠሩበት ቅፅበቶች ወደ ተጋጣሚያቸው የሜዳ አጋማሽ በቶሎ የመግባት ኃላፊነት ይኖርባቸዋል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ክለቦች እስካሁን በሊጉ አራት  ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ደደቢት ሁለት ጊዜ ፋሲል ከነማ ደግሞ አንድ ጊዜ አሸንፈዋል። ቀሪው አንድ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

– ጎንደር ላይ የተደረጉት ሁለቱም ጨዋታዎች በመሸናነፍ የተጠናቀቁ ሲሆን 2009 ላይ ደደቢት 2010 ላይ ደግሞ ፋሲል ከነማ የ1-0 ድል ቀንቷቸዋል።

– ፋሲል ከነማ ዘንድሮ በሜዳው ካደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች አምስት ነጥቦችን ሲያሳካ ሽንፈት አላገኘውም።

– ደደቢት ከትግራይ ስታድየም ውጪ ባደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች በሙል ሽንፈት ሲገጥመው አምስት ግቦችንም አስተናግዷል።

ዳኛ

– ጨዋታው ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ ይመራዋል። ዘንድሮ ሰባተኛው ሳምንት ላይ መቐለ 70 እንደርታን እና ቅዱስ ጊዮርጊስን በመዳኘት የጀመረው ለሚ በዘጠነኛው ሳምንት ድሬዳዋ እና ባህርዳር የተገናኙበትንም ጨዋታ ዳኝቷል። በሁለቱ ጨዋታዎችም ሦስት የመስጠንቀቂያ ካርዶችን ሲመዝ አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ፋሲል ከነማ (4-3-3)

ጀማል ጣሰው        

ሰዒድ ሁሴን – ያሬድ ባየህ – ሙጂብ ቃሲም – አምሳሉ ጥላሁን

ሐብታሙ ተከስተ – ከድር ኩሊባሊ – ኤፍሬም አለሙ

ሱራፌል ዳኛቸው – ኢዙ አዙካ – አብዱራህማን ሙባረክ

ደደቢት (4-2-3-1)

ረሺድ ማታውሲ

መድሀኔ ብርሀኔ – ኤፍሬም ጌታቸው – ክዌኪ አንዶህ – ኄኖክ መርሹ

አብርሀም ታምራት – የአብስራ ተስፋዬ

እንዳለ ከበደ – ዓለምአንተ ካሳ – አቤል እንዳለ

አኩዌር ቻሞ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *