የአሰልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 2-1 ደደቢት

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ8ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ዛሬ ፋሲል ከነማ ደደቢትን አስተናግዶ 2-1 ካሸነፈ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየት ሰጥተዋል። 

”የጨዋታችን ፍሰት እንደጠበቅነው አለመሆኑ ነው ጨዋታውን ከባድ ያደረገው” ውበቱ አባተ – ፋሲል ከነማ

ስለ ጨዋታው

ባለፉት ጨዋታዎች አቻ ነው የወጣነው። ይህ ጨዋታ ደሞ በሜዳችን እንደመሆኑ 3 ነጥብ ለማግኘት ነው ወደ ሜዳ የገባነው። ጥሩ ጨዋታ አርገናል፤ የሚጠበቅብንንም አሳክተናል። ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ጫና የነበረብን ይመስላል። የኛ የጨዋታ ፍሰት እንደጠበቅነው አለመሆኑ ነው ጨዋታውን ከባድ ያደረገው እንጂ በረዣዥም ከሚመጡ ኳሶች ውጪ ያስቸገረን ነገር አልነበረም። የምንፈልገውን አሳክተናል።

ስለ አማራ እና የትግራይ ክልል ክለቦች ጨዋታ

የኛ ክለብ ነው ፈርቀዳጅ ሆኖ የጀመረው። መቐለ ላይ ጥሩ አቀባበል ተደረገልን፤ ጥሩ ተጫውተን በሰላም አጠናቀን ተመለስን። እዚህም በተመሳሳይ ለደደቢት ጥሩ አቀባበል ተደርጎላቸው ጨዋታቸውን በሰላም አጠናቀዋል። በስፖርት ሜዳ ሰላማዊ መንገድ መፈጠሩ እጅግ አስደስቶኛል።


”ከቀደሙ ጨዋታዎቻችን በተሻለ መልኩ ዛሬ ጥሩ ተንቀሳቅሰናል” ኤሊያስ ኢብራሂም – ደደቢት

ስለ ጨዋታው

ከባህርዳር መልስ ከ3 ቀን እረፍት በኋላ ነው የተጫወትነው። እንደ ቡድን ከበፊቱ ጨዋታችን በተሻለ መልኩ ዛሬ ጥሩ ተንቀሳቅሰናል። በነበረን አጨዋወት ደስተኛ ነኝ። በይበልጥ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ጥሩ ነበርን። የጎል እድሎችን ፈጥረናል፤ ጎልም ማስቆጠር ችለን ነበር። እንደ ቡድን ፊት ላይ ያሉብንን ችግር ለመቅረፍ በከፍተኛ ሁኔታ እየሰራን ነው። እዛም ላይ ለውጥ እያመጣን ነው። በቀጣይ የተሻለ እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ።

የፕሮግራም መደራረብ ጫና

ሁለቱንም ጨዋታዎች የምናደርግባቸው ከተሞች እንደመቀራረባቸው መጫወታችን ጥሩ ነው። አንዳንዴ ጨዋታ  ይደራረቡብሃል ፣ ተጫዎቾቻችን በሙሉ  ወጣቶች ናቸው። እንደዚህ አይነት ጫና መቋቋም ላይ ገና ሊሆኑ ይችላሉ እንጂ የጨዋታ መደራረብ ያጋጥምሃል። በችግሮች ማለፍ እንዳለብን ይሰማናል፤ አልፈናልም።

ስለ አቀባበል

ከመጣንበት ቀን ጀምሮ የክለቡ አመራሮች እና የደጋፊ ማኅበሩ ከባህርዳር ድረስ ጥሩ አቀባበል ነው ያረጉልን። ሜዳ ውስጥም ደጋፊዎች የራሳቸውን ቡድን በአግባቡ ነው እንደሚደግፉት ሁሉ የተቃራኒ ቡድንንም ያበረታታሉ፤ በአግባቡ ይቀበላሉ። በዚሁ አጋጣሚ ማመስገን እፈልጋለሁ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *