የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በዚህ ዓመት በእቅድ ከያዛቸው ጉዳዮች አንዱ የሆነው የሊግ ምስረታ ጉዳይ ላይ ለመምከር ከክለቦች ጋር ማክሰኞ በኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ስብሰባ አድርጓል። ጥናታዊ ፅሁፍም የስብሰባው አካል ነበር።
በስብሰባው የፌዴሬሽኑ ዋና እና ምክትል ፕሬዝዳንት የመሩት ሲሆን ከ16ቱ የፕሪምየር ሊግ ክለቦች 11 የሚሆኑት ተወካይ መላካቸው ተገልጿል። ፌዴሬሽኑ ለክለቦቹ ባሳወቀበት ደብዳቤ ፕሬዝዳንቶች እንዲገኙ ቢያሳስብም ጥቂቶቹ ብቻ መገኘታቸው ክለቦቹ ለሊግ ምስረታው የሰጡትኝ ትኩረት ጥያቄ ምልክት ውስጥ እንደሚከተው የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ተናግረዋል። ክለቦቹም በምላሻቸው አብዛኛዎቹ አመራሮች ክለብ ውጪ በሌሎች ዘርፎች ስራ የሚበዛባቸው ከመሆኑ በተጨማሪ በዚህ ውሳኔ በማያስፈልገው የምክክር መድረክ ላይ የመገኘታቸው ፋይዳ እምብዛም በመሆኑ እንደሆነ አስረድተዋል።
ስለ ስብሰባው ምንነት እና ፋይዳ ከክለቦች ጥያቄ ተነስቶም ምላሽ ተሰጥቶበታል። እንዲህ አይነት ከባድ ወሳኔ በተወከልነው ግለሰቦች ብቻ ሊወሰን አይገባም፣ የግሩ ደብዳቤው ዘግይቶ ስለደረሰን በጉዳዩ ላይ ዝግጅት አላደረግንም የሚሉ ጥያቄዎችም ተነስተው አቶ ኢሳይያስ ምላሽ ሰጥተዋል። ” የጠራናችው ዛሬውኑ ሊግ ልንመሰርት አይደለም። ሒደቱ ላይ ለመወያየት ነው። ስለዚህ ፌዴሬሽኑ ጋር መሠረታዊ ችግር የለም። ስሙን፣ አደረጃጀቱን፣ ተግባሩን ራሳችሁ ናችሁ የምትቀርፁት። ይህ ደግም ረጅም ጊዜ ይወስዳል። እናንተ ሊጉን ለመመስረት የሚያስችል ስራ ከሰራችሁ እኛ ፅህፈት ቤት ለመስጠት ዝግጁ ነን። እዚህ ቁጭ ብለን ሊግ እናደራጅላችሁ በሰለን እናንተ ላይ ለመጫን አይደለም የጠራናችሁ። ፍንጭ ለማሳየት ባለሙያ አምጥተናል። በዚህ ሒደት ታልፎ በምታስቀምጡት አቅጣጫ ለቀጣዩ ዓመት ለመስራት ዲዛይን የምታደርጉት እናንተ ናችሁ። ፌዴሬሸኑ ደግሞ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ይህን ማስተባበር ስራው የእኛ ነው። ” ብለዋል።
ከመጀመርያው ክፍል ውይይት በኋላ የፌዴሬሽኑ የጥናት ቡድን ላለፉት አራት ወራት የፌዴሬሽኑን አጠቃላይ መዋቅር ካጠናበት ጥናት መካከል በሊጉ ላይ የሚያተኩረው በአቶ ገዛኸኝ ወልዴ አማካኝነት ቀርቧል። ከ500 በላይ ገፅ ካለው የጥናት ሰነዱ መካከል ከ140 ገፅ በላይ የሚሸፍነው የሊግ አስተዳደር ጉዳዮችን እንደሚሸፍን የገለፁት አቶ ገዛኸኝ ትኩረታቸውን በሊግ አወቃቀር እና ባህርይ እንዲሁም ባለቤትነት ዙርያ አተኩረው ለክለቦቹ ገለፃ አድርገዋል።
በ2014 የዓለም አቀፉ የእግርኳስ አስተዳዳሪ አካል (ፊፋ) በ33 ሀገራት 65 ሊጎች ላይ ያጠናውን ጥናት መነሻ ያደረገ እንደሆነ በተገለፀው ጥናት በፌዴሬሽን ስር እና ራሳቸውን በቻለ ተቋም ስለሚመሰረቱ ሊጎች ማብራርያ ሰጥተዋል።
ጥናቱን መሰረት በማድረግ በፌዴሬሽኑ ስር የሚተዳደሩ እና ራሳቸውን ችለው ኩባንያ በመመስረት የሚቋቋሙ በሚል በሁለት አበይት ክፍሎች የተከፈለ ሲሆን ፌዴሬሽኑ ሙሉ ለሙሉ የሚመራው፣ በፌዴሬሽን ስር ሆኖ ክለቦች ራሳቸውን የሚመሩበት (በፌዴሬሽኑ ፋይናንስ የሚደረግ እና የማይደረግ) በሚል ማብራርያ ተሰጥቶበታል። የፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣልያን፣ ብራዚል፣ ካሜሩን፣ ቱኒዚያ እና አይቮሪኮስት ተሞክሮዎችም ነስተዋል። በሁለተኝነት የተነሳው የአስተዳደር አይነት ክለቦች ራሳቸው ኩባንያ አዋቅረው የሚያስተዳድሩት ነው። የአክሲዮን ድርሻ በመግዛት የሚመሰረት እና እኩል ድርሻ በመከፋፈል የሚመሰረት በሚል የተከፈለው ይህ የአስተዳደር አይነት የእንግሊዝ፣ ጃማይካ እና ደቡብ አፍሪካን ተሞክሮዎች አንስቷል።
ከጥናቱ በመነሳት የሀገራችን ሊግ በፌዴሬሽኑ ስር የሚተዳደር እንደሆነ የገለፁት ጥናት አቅራቢው ይህ አሰራር በበርካታ ሀገሮች የተለመደ ቢሆንም በፌዴሬሽኑ ድክመት ውጤት እንዳላመጣ ገልፀዋል። የራሱ መተዳደርያ ደንብ እና መመርያ የሌለው፣ የክለቦች ተሳትፎ ዝቅተኛ የሆነበት፣ የአማተር አገልጋዮች ብቃት ዝቅተኛ መሆን፣ የገቢ አሰባሰብ እና የቴሌቪዥን ስርጭት የህግ ማዕቀፍ አለመኖር፣ በተያዘ የጊዜ ሰሌዳ አለማከናወን፣ በፖለቲካ ተፅዕኖ ውስጥ መግባት፣ ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ አና ስነዳ አለመኖር ጥሩ ሊግ እንዳይኖረን ካደረጉ ምክንያቶች ውስጥ ተጠቅሰዋል። ክለቦች ራሳቸው ሊግ እንዳያቋቁሙ ተግዳሮት ከሚሆኑ ጉዳዮች መካከል ደግሞ የክለቦች እንደ ክለብ መስፈርት አለማሟላት እንደ ዋና ችግር ተጠቅሷል።
ጥናት አቅራቢው በማጠቃለያቸው ምክረ ሐሳብ ያቀረቡ ሲሆን አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በፌዴሬሽን ስር የሚዋቀር ነገር ግን ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ የክለቦች ተሳትፎ ያደገበት እና ክለቦች ፋይናንስ የሚያደርጉት ሊግ እንዲመሰረት ጥቆማ ሰጥተዋል። ቀስ በቀስም ክለቦች ራሳቸውን እያጎለበቱ በመምጣት ወደ ኩባንያነት እንዲያሳድጉ ምክረ ሐሳባቸውን በማቅረብ የጥናት ገለፃቸውን አጠናቀዋል።
ከጥናቱ መቅረብ በኋላ የክለብ አመራሮች አስተያየት ተከትሏል። የኢትዮጵያ ቡናው መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ የሒደቱን መጀመር በማድነቅ በጀመሩበት ንግግራቸው ጥናቱ መሰራቱ ጥሩ ቢሆንም ለሊግ ምርረታ የሚያበቃ ባለመሆኑ ተጨማሪ ጥናቶች እንደሚያስፈልጉ ገልፀው ከየክለቡ አንድ አንድ ግለሰብ ተውጣጦ የሚመሰረተው ኮሚቴ በቂ እንዳልሆነ ተናግዋል። ሊግ ከመመስረቱ በፊትም ተዟዙሮ የመጫወት ጥቅም እና ጉዳት እንዲሁም የክለቦች ከመንግስት ጥገኝነት መላቀቅ ጉዳይ መቅደም ይርበታል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የሲዳማ ቡናው አቶ መንግስቱ ሳሳሞ በበኩላቸው ለኛ ሀገር ይስማማል ተብሎ የቀረበው (በፌዴሬሽን ስር መተዳደር) ምክረ ሐሳብ የተደረገፈው በእግርኳስ ዝቅተኛ ደረጃ ያላቸው ሀገራት ላይ በተሰራ ጥናት ነው የሚል አሰነያየት ሲሰጡ የፋሲል ከነማ ስራ አስኪያጅ ደግሞ ክለቦች የመንግስት በመሆናቸው ምክንያት የመንግስት ሚና በግልፅ መቀመጥ እንዳለበት ሀሳብ አቅርበዋል። ተዟዙሮ መጫወት ሊደገፍ የሚገባው ሀሳብ መሆኑን ያነሱት ስራ አስኪያጁ ከሀገር አልፎ የጎረቤት ሀገራት ቢካከተቱበትም ፋይዳው ከፍ ይላል ብለዋል። ሊጉ በድርሻ ክፍፍል ከተመሰረተ የሚወጡ እና የሚወርዱ ክለቦች በምን መልኩ ይስተናገዳሉ የሚል ጥያቄም አቅርበዋል።
ከድሬዳዋ ከተማ ፕሬዝዳንት ጥናቱ ችግሮች እንዴት እንደሚፈቱ እና ምክረ ሐሳብ በማቅረብ ረገድ ድክመት እንዳለበት ገለፀው ለማቋቋም ያለው የ7 ወር ጊዜ እና የኮሚቴው በ16 ሰዎች መዋቀር በቂ እንዳልሆነ ተናግረዋል። ከአዳማ ከተማ ስራ አስኪያጅ አቶ አንበሴ በተሰጠው አስተያየት ደግሞ ጥናቱ እንዴት መሬትወርዶ ይሰራል የሚለውን እንዳልዳሰሰ ገለፀው ቀጣይነት ያለው እድገት የሚያመጣ አደረጃጀት መቀመጥ አንዳለበት ገልፀዋል። የመቐለ ስራ አስኪያጅ አቶ ሽፈራው በበኩላቸው ጥናቱ ግላዊነት እንዳያመዝንበት ስጋታቸውን ገልፀው ገና ጀማሪ በመሆናችን መነሻ ካፒታል መንግስት ማቅረብ እንዳለበትም ገልፀዋል።
ከአስተያየቶቹ በመቀጠል የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት የማጠቃለያ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ወደ ትግበራ ሒደት ለማምራትም እስከ ጥር 14 ድረስ ክለቦች የሚወክሏቸውን ግለሰቦች ለፌዴሬሽኑ እንዲያሳውቁ በማሳሰብ ስብሰባው ተጠናቋል።