ከ11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል ድሬዳዋን ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያገናኘውን ጨዋታ የተመለከተው ዳሰሳችንን እንሆ።
ከአዳማ በሽንፈት የተመለሰው ድሬዳዋ ከተማ ነገ ቅዱስ ጊዮርጊስን ያስተናግዳል። 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ብርቱካናማዎቹ ከስምንት ጨዋታዎች ዘጠኝ ነጥቦችን ብቻ ነው ያሳኩት። ከሁለት አቻ ውጤቶች በኋላ ባህር ዳርን ባስተናገዱበት ጨዋታ ያሳኩት ድል ወደ አሸናፊነት የሚመልሳቸው ቢመስልም በአዳማ 1-0 መሸነፋቸው አልቀረም። ከሲዳማው ሽንፈት በኋላ በሊጉ መሻሻልን እያሳየ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንፃሩ ተከታታይ ድሉን ያሳካበትን ሳምንት ነበር ያሳለፈው። ከኢትዮጵያ ዋንጫ ያስወጣው መከላከያን በሰፊ የግብ ልዩነት የረታበት ጨዋታም ወደ ሦስተኛ ደረጃ ከፍ እንዲል ረድቶታል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ነገ ድል ከቀናው በዘንድሮው ውድድር ሦስት ተከታታይ ድል በማሳካት ከአዳማ ቀጥሎ ሁለተኛው ቡድን መሆን ሲችል ድሬዳዋም ውጤት ከቀናው ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች እያሉት ከአደጋው ዞን በመጠኑም ቢሆን የመራቅ ዕድል ይኖረዋል።
ድሬዳዋ ከተማ ዘነበ ከበደ እና ኃይሌ እሸቱን ከጉዳት መልስ የሚያገኝ ሲሆን ራምኬል ሎክ ግን አሁንም ወደ ሜዳ የማይመለስ ይሆናል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ደግሞ ከሳምንታት በፊት ጉዳት የገጠማቸው ምንተስኖት አዳነ እና መሀሪ መና እንዲሁም አቤል ያለው አለማገገማቸው ታውቋል።
ጥሩ የመከላከል አቅም ያለው ድሬዳዋ ነገ የቅዱስ ጊዮርጊስን የጥቃት መስመሮች መዝጋት ላይ ትኩረት እንደሚያደግ ይጠበቃል። ሆኖም ቡድኑ በመልሶ ማጥቃት የሚያገኛቸው አጋጣሚዎችን ወደ ግብነት የመቀየር ድክመቱን አርሞ መግባት የግድ ይለዋል። በመሆኑም የአጥቂ መስመር ጥምረቱ ላይ ለውጦች ሊያደርግ የሚችልበት ዕድል ይኖራል። ከዚህ ውጪ በመከላከያው ጨዋታ የሰመረ የሚመስለው የሳላሀዲን እና ጌታነህ ጥምረት ከድሬ የኋላ መስመር ጋር ብርቱ ፍልሚያ ይጠብቀዋል። የጊዮርጊሱ የጨዋታ አቀጣጣይ ታደለ መንገሻ ከፍሬድ ሙሸንዲ እንዲሁም የቡድኑ ወሳኝ የጥቃት መነሻዎች የሆኑት የመስመር ተመላላሾች ከባለሜዳዎቹ የግራ እና ቀኝ የአማካይ እና የተከላይ ክፍል ተሰላፊዎች ጋር የሚኗራቸው ግንኙነት የጨዋታውን ውጤት የመወሰን አቅሙ ከፍ ያለ ነው።
የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– ሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ 14 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 9 በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ ድሬዳዋ ከተማ 3 አሸንፏል፡፡ ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ጊዮርጊስ 25 ጎሎችን ሲያስቆጥር ድሬዳዋ 12 ጎሎች አሉት።
– ድሬደዋ ላይ 7 ጨዋታዎች ተደርገው እኩል 3 ጊዜ ድልን ተቋድሰዋል፡፡ አንዱ ጨዋታ ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
– አምና በሁለቱ ቡድኖች መካከል የተደረጉት ሁለቱም ጨዋታዎች በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ነበር።
– ድሬዳዋ ከተማ እስካሁን ያገኛቸውን ሁለት ድሎች ሜዳው ላይ ሲሆን ያሳካው ከአራት ጨዋታዎች ሽንፈት ያገኘው አንድ ጊዜ ብቻ ነው።
– ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ክልል ስታድየሞች ከተጓዘባቸው ሦስት አጋጣሚዎች አራት ነጥቦችን ሲያሳካ በድል የተመለሰው ከመጨረሻው የደቡብ ፖሊሱ ጨዋታ ነበር።
ዳኛ
– በሦስት ጨዋታዎች 13 የቢጫ ካርዶችን እና አንድ የፍፁም ቅጣት ምት የሰጠው ኢንተርናችናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ይህን ጨዋታ እንዲመራ ተመድቧል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ድሬዳዋ ከተማ (4-4-2)
ሳምሶን አሰፋ
ገናናው ረጋሳ – አንተነህ ተስፋዬ – ፍቃዱ ደነቀ – ሳሙኤል ዮሃንስ
ሚኪያስ ግርማ – ፍሬድ ሙሺንዲ – ምንያህል ይመር – ረመዳን ናስር
ሐብታሙ ወልዴ – ሲላ አብዱላሂ
ቅዱስ ጊዮርጊስ (3-5-2)
ፓትሪክ ማታሲ
ሳላለዲን በርጌቾ – አስቻለው ታመነ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ
በኃይሉ አሰፋ – ሙሉዓለም መስፍን – ናትናኤል ዘለቀ – ኄኖክ አዱኛ
ታደለ መንገሻ
ሳላሀዲን ሰዒድ – ጌታነህ ከበደ