ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ በሬችሞንድ አዶንጎ ብቸኛ ግብ ባህር ዳር ከተማን በማሸነፍ ከሽንፈት እና ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ወደ ድል ተመልሷል።
ባለሜዳዎቹ ወልዋሎዎች ባለፈው ሳምንት ከሜዳው ውጭ ከ.ወላይታ ድቻ አቻ ወጥቶ ከተመለሰው ስብስባቸው ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ሲገቡ በአንፃሩ እንግዶቹ የጣና ሞገዶች ባለፈው ሳምንት ደደቢት ካሸነፈው ስብስባቸው ዳንኤል ኃይሉን ደረጄ መንግስቱ ቀይረው ወደ ሜዳ ገብተዋል።
አቶ አንገሶም ካሕሳይ እና አቶ ክንደያ ገ/ህይወትን (ፕሮፌሰር) ጨምሮ በርካታ የክብር እንግዶች ያስጀመሩት ጨዋታ በባለሜዳዎቹ ወልዋሎዎች ሙሉ ብልጫ ሲጀምር እንግዶቹ ባህርዳር ከተማዎች በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ተረጋግተው መጫወት ተስኗቸው ለበርካታ ስህተቶች ሲዳረጉ ተስተውልዋል። ለወትሮ የሚታወቁበትን የተለጠጡ የአጥቂ ክፍል ተጫዋቾቻቸው ላይ የተመሰረተ አጨዋወት የተከተሉት ቢጫ ለባሾቹ የተጠቀሰው አጨዋወት በአራቱ የባህር ዳር ተከላካዮች መካከል የፈጠረው ክፍተት እና በግል ተከላካዮቹ በሚሰሩት ስህተት ተጠቅመው በርካታ የግብ አጋጣሚዎችን ማግኘት ችለዋል።
እንቅስቃሴው አማካኝነት በቂ የመጫወቻ ክፍተት ያገኘው ጋናዊው አጥቂ ሬችሞንድ አዶንጎ በርካታ የግብ እድሎች ፈጥሯል። በመስመር ገብቶ ለኤፍሬም አሻሞ አቀብሎት ኤፍሬም መትቶ ሃሪሰን በግሩም ሁኔታ ያወጣው እና ከረጅም ርቀት የተላከለትን ኳስ አብርዶ ለአፈወርቅ ሰጥቶት አማካዩ ያልተጠቀመበት ኳስ ወልዋሎዎች ከፈጠሯቸው ዕድሎች መካከል ይጠቀሳሉ። ወልዋሎች በጨዋታው ባልተለመደ መልኩ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በቁጥር በዝተው እና ቀርበው ለመጫወት የሞከሩ ሲሆን አፈወርቅ ኃይሉ ከአዶንጎ ጋር በአንድ ሁለት ቅብብል በመግባት አክርሮ መትቶ ሃሪሰን ሄሱ ያዳናት እንዲሁም ደስታ ደሙ እና ፕሪንስ ሰቨሪንሆ ከርቀት ያደረጓቸው ሙከራዎችም በዚህ አጋማሽ የሚጠቅስላቸው ነበር።
ከተጋጣሚው ወልዋሎ በተቃራኒው አጥበው በሚያጠቁ የመስመር ተጫዋቾቹ እና ለብቸኛ አጥቂው ጃኮ አረፋት በሚሻገሩ ረጃጅም ኳሶች ለማጥቃት የሞከሩት ባህር ዳር ከተማዎች ምንም እንኳ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ካሳዩት ያለመናበብ አገግመው ወደ ጨዋታው እንቅስቃሴ ቢገቡም የወልዋሎ ተከላካዮችን አልፈው ንፁህ የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም። ሆኖም ግርማ ዲሳሳ እና ጃኮ አረፋት ከርቀት መትተው ግብ ጠባቂው አብዱልዓዚዝ ኬይታን ያልፈተኑ የግብ ሙከራዎች ሲያደርጉ ደረጀ መንግስቱ ከመስመር የተሻማችውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ያደረጋት ሙከራ ባህርዳር ከተማዎች በመጀመርያው አጋማሽ ከፈጠሯቸው ዕድሎች የተሻለ ለግብ የቀረበች ነበረች።
በሰላሳ ሰባተኛው ደቂቃ ላይ በባህር ዳር ከተማ ሳጥን ውስጥ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ሬችሞንድ አዶንጎ አስቆጥሮ ወልዋሎ እየመራ ወደ ዕረፍት እንዲያመራ አስችሎታል።
ከመጀመርያው አጋማሽ በተለየ ብርቱ ፉክክር እና ጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ጥቂት የግብ ሙከራዎች የታየበት ቢሆንም በብዙ መለኪያዎች ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ ነበር። ግርማ ዲሳሳ በግሩም ሁኔታ ያሻገረው ኳስ ከግቡ አቅራብያ የነበረው ወሰኑ ዓሊ ሳይደርስበት ወደ ውጭ በወጣው ሙከራ የጀመረው ሁለተኛው አጋማሽ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች የባህርዳር ከተማዎች ብልጫ ቢታይበትም ብልጫው ለብዙ ደቂቃዎች ያልቆየ እና ንፁህ የግብ ዕድል የፈጠረ አልነበረም። በአንፃሩ አጨዋወታቸው ቀጥተኛ በማድረግ ወደ አጥቂያቸው ሬችሞንድ አዶንጎ ላይ የተመሰረተ አጨዋወት መከተል የመረጡት ወልዋሎዎች ከቆሙ ኳሶች ሁለት ያለቀላቸው እድሎች ፈጥረው ነበር። በተለይም ፕሪንስ ሰቨሪንሆ አሻምቷት ደስታ ደሙ ጨርፎ ያደረጋት የግብ ሙከራ እጅግ ለጎል የቀረበች ነበረች።
ሁለት ቅያሪዎች በማድረግ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው ለመጫወት የሞከሩት ባህር ዳር ከተሞዎችም በርካታ የግብ እድሎች ፈጥረው ነበር። ማራኪ ወርቁ ከርቀት አክርሮ መትቶ ከአግዳዊው ወደ ላይ ለጥቂት የወጣችበት ፣ አስናቀ ከቅጣት ምት ያሻማትን ኳስ ተጠቅሞ ኤልያስ አህመድ ያደረጋት ሙከራ እና ጃኮ አረፋት በግንባሩ ገጭቶ ያደረጋት ጥሩ ሙከራ የጣና ሞገዶችን አቻ ለማድረግ ከተቃረቡ ሙከራዎች መካከል ነበሩ። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በእጃቸው የገባው ሶስት ነጥብ ላለማጣት አፈግፍገው የተጫወቱት ወልዋሎች በበኩላቸው በብርሃኑ አሻሞ አማካኝነት ጥሩ መከራ አድርገው ነበር።
ጨዋታው በዚህ መልኩ መጠናቀቁ ተከትሎ ወልዋሎዎች ከሶስት ጨዋታ በኋላ ድል ሲያስመዘግቡ ባህርዳር ከተማዎች የዓመቱ ሁለተኛ ሽንፈታቸው ሆኖ ተመዝግቧል።
ከጨዋታው መጠናቀቀ በኋላ የወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ደጋፊዎች ግንባታው የቆወሙ የከተማቸው ስቴድየም እንዲቀጥል ለሰላሳ ደቂቃ ያክል በስቴድየም ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ ጥያቄያቸው አቅርበዋል