የአሰልጣኞች አስተያየት | መከላከያ 2 2 ስሑል ሽረ

ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድየም 04፡00 ላይ በተደረገ የፕሪምየር ሊጉ 11ኛ ሳምንት ጨዋታ መከላከያ እና ስሐል ሽረ 2-2 ተለያይተዋል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።

” አሁንም ያገኘናቸውን ዕድሎች መጠቀም ላይ ችግር አለብን ” ዳንኤል ፀሀዬ – ስሑል ሽረ

ስለጨዋታው

” ተጭነን ለመጫወት ነበር የገባነው ፤ በተለይም በመጀመሪያዎቹ ሃያ ደቂቃዎች። ግብም በቶሎ አግኝተናል ሆኖም ከዛ በኋላ ወደ ኋላ በመሸሻችን ክፍተቶችን ፈጥረን ኳሱን ሊይዙት ችለዋል ፤ ያገኙትንም ዕድል ተጠቀዋል። በርግጥ የሳቷቸው ኳሶች አሉ እኛም በልደቱ አማካይነት ሁለተኛ ግብ የሚሆን ንፁህ የግብ ዕድል አግኝተን ነበር። ያን ብንጠቀም ጨዋታውን መጨረስ እንችል ነበር።”

ስለተደረጉ ለውጦች

” የጀመርነው በ3-4-1-2 ወደ ከዛ በኋላ ግን የሚጣሉ ኳሶች ስለበዙ በ4-5-1 ነበር የተጫወትነው። በቅርብ እየተገናኙ ስለነበር ከዚያ በኋላ የኳስ ንክኪያቸውን ለማቋረጥ እና ብልጫ ለመውሰድ ችለናል። ጎል ማስቆጠር የምንችልባቸውን ዕድሎችም ፈጥረን ነበር። ”

ስለቡድኑ አጥቂዎች እንቅስቃሴ

” አጥቂዎቻችን ጥሩ ናቸው። ግን አሁንም ያገኘናቸውን ዕድሎች መጠቀም ላይ ችግር አለብን። በየጨዋታው ወደ ግብ ብንደርስም ይህ ችግራችን ግብ እንዳናስቆጥር አድርጎናል። ዛሬ ያደረጉት እንቅስቃሴ ግን ጥሩ ነው። ”

“ውጤቱ የሚገባን አይደለም ፤ በጣም አዝኛለው” ሥዩም ከበደ – መከላከያ

ስለጨዋታው

” ውጤቱ የሚገባን አይደለም ፤ በጣም አዝኛለው። ዛሬ ሙሉ ነጥብ ይዘን ለመውጣት ሳምንቱን ሙሉ ተራርመን ነው የቀረብነው። በብዙ ነገር እንሻል ነበር ብዬም አስባለው። ጨዋታው እንደጀመረ በኛ ስህተት ነበር ግብ የተቆጠረብን። እንደዚያም ሆኖ ውጤቱን ለመቀልበስ አጥቅተን ተጫውተን አቻ መሆን ችለን ነበር። ከዕረፍት መልስም ተጭነን ተጫውተን መርተናል። ከዚያ በኋላ ማጥቃት እና መከላከሉን ማመጣጠን ይገባን ነበር። በፈጠርነው ክፍተት የተቆጠረብን ጎል ግን ይበልጥ አውርዶናል። ለነሱ ከሜደ ውጪም ስለሆነ ትልቅ ውጤት ነው። ወደራሳችን ተመልሰንም በቀጣይ የምናስተካክላቸው ነገሮች ይኖራሉ። ”

ስለ ሽመልስ ጉዳት

” ሽመለስ ራሱ ነው ቀይሩኝ ያለው ፤ ከዚህ በፊትም በልምምድ ላይ ጉዳት ላይ ነበር። ባለፈውም ጨዋታ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ እንዲገባ ፍላጎት ነበረኝ ‘ተቀይሬ ብገባ ይሻላል ይሰማኛል’ ስላለ ነው። አሁን ያለበትን ሁኔታ ለማወቅ ግን የህክምና ሪፖርቱን ማየት ይኖርብኛል። “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *