የፕሪሚየር ሊጉ 2ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትላንት እና ከትላንት በስቲያ ተደርገዋል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም ጨዋታዎቹን ተንተርሳ ያሰናዳችውን እውነታ እንዲህ አቅርባለች፡፡

 

– በ2ኛው ሳምንት 13 ግቦች ከመረብ አርፈዋል፡፡ ከመጀመርያው ሳምንትም በ2 ግቦች ብልጫ አሳይቷል፡፡ በአጠቃላይ በሁለቱ ሳምንት ከተቆጠሩ 24 ግቦች ስድስቱ ከፍፁም ቅጣት ምት የተገኙ ናቸው፡፡

– ዳሽን ቢራ እና አዳማ ከነማ ሁለቱንም ጨዋታ በማሸነፍ ብቸኛ ሲሆኑ ግብ ያላስተናገዱ ቡድኖች በመሆንም ብቸኞቹ ናቸው፡፡ ባንክ እና ሆሳዕና ምንም ግብ ያላስመዘገቡ ቡድኖች ሲሆኑ ሀዋሳ ከነማ ሁለቱንም ጨዋታ በአቻ ውጤት ያጠናቀቀ ቡድን ሆኗል፡፡

– አዳማ ከነማ በሜዳው አልበገር ብሏል፡፡ ወደ ሞቃታማዋ ከተማ የሚመጡ ቡድኖችም በሽንፈት መመለሳቸው እየተለመደ መጥቷል፡፡ የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ቡድን ካለፉት 7 ተከታታይ የሜዳው ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው 21 ነጥብ 18 አሳክቷል፡፡ (6 ድል እና 1 ሽንፈት)

– ቅዱስ ጊዮርጊስ በሲዳማ ቡና ላይ ያለውን የበላይነት ያስጠበቀበትን ውጤት ትላንት አስመዝግቧል፡፡ ሲዳማ በ2002 ወደ ዋናው ሊግ ካደገ ወዲህ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባደረጋቸው 13 ጨዋታዎች ምንም ድል ማስመዝገብ አልቻለም፡፡ 9 ጨዋታዎች በጊዮርጊስ አሸናፊነት ሲጠናቀቁ 4 ጨዋታዎች ካለ ግብ 0-0 ተጠናቀዋል፡፡

– የቀድሞዋ የእግርኳስ ከተማ ድሬዳዋ ከ3 አመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ አስተናግዳለች፡፡ ድሬዳዋ ከነማ በሜዳው ለመጨረሻ ጊዜ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ የተጫወተው በግንቦት 2004 (24ኛ ሳምንት) አየር ኃይን 4-2 የረታበት ነው፡፡

– ሀዋሳ ከነማ ወደ ድሬዳዋ የሚያደርገው ጉዞ ፈታኝ ሆኖበታል፡፡ በ1994 ምድር ባቡርን 3-0 ካሸነፈ ወዲህ ከድሬዳዋ በድል ተመልሶ አያውቅም፡፡ በአጠቃላይ በድሬዳዋ ካደረጋቸው 13 ጨዋታዎችም ያሸነፈው 3 ብቻ ነው፡፡

– ትላንት በሜዳው በታሪኩ የመጀመርያ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ያደረገው አዲስ መጪው ሀዲያ ሆሳዕና መጥፎ አጀማመር አድርጓል፡፡ ዘንድሮ ሁለቱንም ጨዋታ የተሸነፈ ብቸኛው የፕሪሚየር ሊግ ቡድንም ሆኗል፡፡ ሌሎቹ ቡድኖች ከሁለት ጨዋታዎች ቢያንስ አንድ ነጥብ አግኝተዋል፡፡

– እሁድ እለት ካለግብ አቻ የተለያዩት ደደቢት እና ባንክ በአንደኛው ዙር ተከባብሮ በመውጣት ልምዳቸው ቀጥለዋል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች በአስገራሚ ሁኔታ ባለፉት 6 ተከታታይ የአንደኛው ዙር ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ ያለፉት 4 ተከታታይ የአንደኛ ዙር ግንኙነታቸው 0-0 የተጠናቀቁ ናቸው፡፡ አሰልቺው ጨዋታ?

– መከላከያ በሊጉ ከ5 ድል አልባ ጉዞ በኋላ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል፡፡ ጦሩ የመጨረሻ የፕሪሚየር ሊግ ድሉ በየካቲት ወር መልካ ቆሌ ላይ ወልድያን 1-0 ያሸነፈበት ነው፡፡

– ወላይታ ድቻ ከ5 ጨዋታ በኋላ አርባምንጭ ከነማን 1-0 በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሷል፡፡ ድቻ ባለፉት 5 ጨዋታዎች 2 የአቻ ውጤቶች እና 3 ሽንፈት አጋጥሞታል፡፡

– ወላይታ ድቻ በፕሪሚየር ሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ አርባምንጭ ከነማን ድል አድርጓል፡፡ ከትላንቱ ጨዋታ በፊት 4 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን 3 ጊዜ አቻ ተለያይተው አርባምንጭ አንድ ጊዜ ድል ቀንቶታል፡፡ አርባምንጭ እና ወላይታ ድቻ አምናም በተመሳሳይ 2ኛ ሳምንት ላይ ነበር የተገናኙት፡፡

– ሲዳማ ቡና በአስከፊ ግስጋሴው ቀጥሏል፡፡ አምና በ19ኛው ሳምንት ደደቢትን በሜዳው 2-1 ካሸነፈ ወዲህም 3 ነጥብ ማሳካት ተስኖታል፡፡ በ9 ጨዋታዎች (የትላንቱን ጨምሮ) 6 ሲሸነፍ 3 አቻ ተለያይቷል፡፡ ከጥር ወር ወዲህ ደግሞ ምንም ከሜዳ ውጪ ድል ማስመዝገብ አልቻለም፡፡

– ኤሌክትሪክ ከ3 ጨዋታ ተከታታይ ድል በኋላ ሽንፈት አጋጥሞታል፡፡ አምና ለመጨረሻ ጊዜ የተሸነፈው እሁድ እለት በረታው አዳማ ከነማ ነበር፡፡ (1-0)

ያጋሩ