ከሞሮኮው ሀሳኒያ አጋዲር ጋር የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ሁለተኛ ዙር የመልስ ጨዋታውን ዛሬ ምሽት ያድረገው ጅማ አባ ጅፋር በድምር ውጤት 5-0 ተሸንፎ ከውድድሩ ውጪ ሆኗል።
አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ከተደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ሁለቱም ክለቦች ሁለት ሁለት ለውጦችን አድርገው ነበር የዛሬውን ጨዋታ የጀመሩት። በዚህም ጅማ አባ ጅፋር በኤልያስ ማሞ እና አስቻለው ግርማ ምትክ ይሁን እንዳሻው እና ቢስማር አፒያን ሲጠቀም አጋዲሮች በአብዱልከሪም ባዲ እና ኢማድ ኪማዊ ምትክ ጃላት ዳውዲ እና አይቡ ቃስሚን ወደ ሜዳ አስገብተዋል።
ጨዋታው እንደጀመረ አጋዲሮች በአዲስ አበባ ስታድየሙ ጨዋታ ድንቅ ግብ ባስቆጠረው ዞሂር ቻውች አማካይነት በጅማ ሳጥን ቀኝ አቅጣጫ ውስጥ ሙከራ ቢያደርጉም ቀጣዮቹ ደቂቃዎች ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የታየባቸው ነበሩ። ሁለቱም ቡድኖች ወደ ግብ በመድረስ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱም ታይቷል። ነገር ግን ኳስ እና መረብን ለማገናኘት የታደሉት ባለሜዳዎቹ አጋዲሮች ነበሩ። 18ኛው ደቂቃ ላይ ባድር ካቻኒ እና ሶፋኒ ቦፍቲኒ ከማዕዘን ምት ተቀባብለው ካቻኒ ያሻማውን ኳስ ያሲን ራሚ ራሱን ነፃ በማድረግ በግንባሩ ባስቆጠረው ኳስ ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል። ከደቂቃዎች በኋላ አጋዲሮች ከቅጣት ምት ባሻገሩት ኳስ ሌላ አደጋ ለመፍጠር ተቃርበው ነበር።
ከግቡ በኋላ ጅማ አባ ጅፋሮች ኳስ ይዘው በመጫወት ወደ አጋዲሮች የግብ ክልል ለመድረስ ሲጥሩ ታይተዋል። ነገር ግን ጥረታቸው ከሜዳው አጋማሽ እምብዛም ሳይዘልቅ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠርም በቂ ሳይሆን ቀርቷል። ከዛ ይልቅ ጨዋታዉን አቀዝቅዘው በድንገተኛ ጥቃቶች ወደ ጅማ ሜዳ ለመግባት ይጥሩ የነበሩት አጋድሮች ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገዋል። 32ኛው ደቂቃ ላይ ዞሂር ቻውች ከሚሮስላቭ ማርኮቪች የተቀበለውን ኳስ ከርቀት ሞክሮ ዳንኤል አጃዬ አድኖበታል። አራት ተቀያሪ ተጫዋቾች ብቻ ይዘው የተጓዙት ጅማዎች በአዳማ ሲሶኮ ላይ ደርሶ የነበረው ጉዳት ቅያሪ ለማድረግ የሚያስገድዳቸው ቢመስልም ተጫዋቹ አገግሞ ተመልሷል። ሆኖም ቡድኑ አንድም ሙከራ ሳያደርግ ጨዋታው ወደ ዕረፍት አምርቷል።
ሁለተኛው አጋማሽ ቀዝቀዝ ባለ እንቅስቃሴ የጀመረ ቢሆንም ባለሜዳዎች በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ውስጥ መሪነታቸውን ወደ ሥስት አስፍተዋል። 53ኛው ደቂቃ ላይ ሶፋኒ ቦፍቲኒ ከማዕዘን ምት የተሻገረለትን ኳስ በመግጨት ሲያስቆጥር ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ከግራ መስመር ዞሂር ቻውች ያሻገረለትን ሰርቢያዊው የመስመር አጥቂ ሚሮስላቭ ማርኮቪች ወደ ግብነት ቀይሮታል። በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ጅማዎች የተሻለ መነቃቃት በማሳየት ወደ አጋዲሮች የግብ ክልል መድረስ ችለው ነበር። 59ኛው ደቂቃ ላይ ተስፋዬ መላኩ የአጋዲር ተጫዋቾችን አልፎ ሳጥን ውስጥ ለዲዲዬ ለብሪ የሰጠውን ኳስ ተከላካዮች ሲያወጡት በአንድ ደቂቃ ልዩነት ደግሞ ቢስማርክ አፒያ ዲዲዬ ለብሪ ከግራ መስመር በሰጠው ኳስ ከግብ ጠባቂው ጋር ቢገናኝም ሙከራው ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል።
ጅማዎች በተመሳሳይ መንገድ ኳስ ይዘው ወደ ፊት ለመጠጋት ጥረታቸውን ቢቀጥሉም ከ70ኛው ደቂቃ በኋላ ድካም እየታየባቸው መጥቷል። አጋዲሮችም 73ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልሀኪም ባሳኒ ለአህመድ ውሪዳት በሰጠው ኳስ አራተኛ ግብ ለማስቆጠር ቢቃረቡም ተቀይሮ የገባው ውሪዳት ያደረገው ሙከራ በማይታመን መልኩ ወደ ውጪ ወጥቷል። ሌላው ተቀያሪ አብዱል ላሊ ካንቦቢ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ከዳንኤል አጃዬ ጋር ፊት ለፊት የተገናኘበትን አጋጣሚ ግን ቀለል ባለ አጨራረስ የቡድኑን አራተኛ ግብ ማስቆጠሩ አልቀረም። በጅማ አባ ጅፋር በኩል ከቡድኑ መዳከም አንፃር እጅግ በዘገዩ ቅያሪዎች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ኤልያስ ማሞ እና ኤርሚያስ ኃይሉን ተቀይረው የገቡ ቢሆንም ቡድኑ የጎላ ለውጥ ማምጣት ሳይችል ጨዋታው በአጋዲሮች 4-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በዚህም መሰረት ጅማ አባ ጅፋር በ5-0 ድምር ውጤት ከአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ውጪ ሆኗል።