በኤርትራ አስተናጋጅነት የሚካሄደው የሠላም እና የወዳጅነት ዋንጫ የካቲት መጀመርያ ላይ እንደሚካሄድ የኤርትራ እግርኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ነጋሽ ተክሊት ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጸዋል።
ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ ወጣት ቡድኖች የሚሳተፉበትና ለመጀመርያ ጊዜ የሚካሄደው ‘የሠላም እና ወዳጅነት ዋንጫ’ በአስመራ ከተማ እንደሚካሄድ ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወቃል። በዚህ የአራቱን ሃገራት ወዳጅነት ለማጠናከር እና የዞኑን የእግርኳስ ትስስር ለማጠናከር ታስቦ የሚካሄደው ውድድር አስመራ ከተማ ላይ ከየካቲት ጀምሮ ይካሄዳል።
ውድድሩን አስመልክቶ የአስተናጋጅ ሀገር ምክትል ፕሬዝደንት የሆኑት የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የኤርትራ ጫማ ክለብ አጥቂ እንዲሁም የኤርትራ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበሩት ነጋሽ ተክሊት ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በስልክ ባደረጉት አጭር ቆይታ ይህን ተናግረዋል።
” ውድድሩ መዘጋጀቱ ጠቀሜታው የጎላ ነው። የሀገራቱን ሠላም፣ ወዳጅነት ለማጠናከር ከማስቻሉ ባሻገር የእግርኳስ ደረጃቸውን ከፍ ለማድረግ ይረዳል። እስካሁን አራቱም ሀገሮች (ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ እና ኤርትራ) በውድድሩ ላይ እንደሚካፈሉ ተረጋግጧል። ውድድሩንም በኢትዮጵያ አቆጣጠር የካቲት ስምንት ለመጀመር አስበን ተዘጋጅተናል። በአጠቃላይ የውድድሩ ጊዜ እየቀረበ ሲመጣ በውድድሩ ዙርያ የሚኖሩ መረጃዎችን እያሳወቅን እንሄዳለን።” ብለዋል።