የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዝዮን ዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ የተጠበቀው የንግድ ባንክ እና አዳማ ከተማ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተፈፅሟል። መከላከያ እና ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ ማሸነፍ ችለዋል።
የአዲስ አበባ ስታድየም ውሎ
በሁለት ነጥቦች ልዩነት ተከታትለው በሠንጠረዡ አናት ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አዳማ ከተማ የሳምንቱን ተጠባቂ ጨዋታ 08:00 ላይ አድርገው ያለ ጎል አቻ ተለያይተዋል። በጥሩ የኳስ ፍሰት በተጀመረው ጨዋታ ንግድ ባንኮች ኳስ መስርቶ ለመጫወት ሲያደርጉት የነበረውን ተደጋጋሚ ጥረት አዳማዎች በፍጥነት በመቀማት ሲያቋርጡት ተስተውሏል። በዚህም ባንኮች ወደ አዳማ የግብ ክልል የደረሱት በጥቂት አጋጣሚዎች ነበር። በ20ኛው ደቂቃ ረሒማ ዘርጋው ከርቀት በመምታት የሞከረችውና ኢላማውን ስቶ የወጣው ኳስ ብቸኛው የግበ አጋጣሚ ነበር።
እንግዶቹ አዳማዎች የባንክን እንቅስቃሴ በማበላሸት እና በፈጣን ቅብብሎሽ ረገድ ጥሩ ቢሆኑም ከፊት የተጣመሩት ሴናፍ እና ሰርክአዲስ እርስ በእርስም ሆነ ከአማካዮች ጋር ባላቸው ግንኙነት ተራርቀው ሲጫወቱ የኘነበረ በመሆኑ እንደ ባንክ ሁሉ በዚህ አጋማሽ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ በእጅጉ ተቸግረዋል። በ32ኛው ደቂቃ እጸገነት ከማዕዘን ምት የተሻገረላትን ኳስ ሞክራ ወደ ውጪ የወጣባት ሙከራም ብቸኛ የሚጠቀስ አጋጣሚ ነበር።
ከመጀመርያው ጋር ተመሳሳይ እንቅስቃሴ በታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ግልፅ የሆነ የጎል እድል በመፍጠር በኩል ተቸግረው ታይተዋል። የተጫዋቾች የግል ጥረት ካልሆነ በቀር እንደቡድን የተደራጀ የማጥቃት እንቅስቃሴም መመልከት አልተቻለም። በ52ኛው ደቂቃ ሰርክአዲስ ጉታ (አዳማ) ከግራ የሳጥኑ ክፍል መትታ የጎሉ ቋሚ የመለሰባት፣ በ60ኛው ደቂቃ ሽታዬ ሲሳይ (ባንክ) ከግማሽ ጨረቃ መትታ አግዳሚው የመለሰባት እና በ72ኛው ደቂቃ ሰናይት ቦጋለ (አዳማ) በተመሳሳይ ከግማሽ ጨረቃ ሞክራ ወደ ውጪ የወጣባት ሙከራዎች ለዚህ እንደማሳያ የሚታዩ ናቸው።
ጨዋታው ያለጎል መጠናቀቁን ተከትሎ በሁለቱ መካከል የነበረው የሁለት ነጥቦች ልዩነት እንደተጠበቀ በደረጃ ሠንጠረዡ አናት ተከታትለው ተቀምጠዋል።
10:00 ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን የገጠመው መከላከያ በቀላሉ 3-0 በማሸነፍ ከአዳማ ጋር ነጥቡን አስተካክሏል። በመጀመርያ የኳስ ንክኪ የጊዮርጊሷ ፋና ዘነበ በግራ መስመር በኩል አምልጣ በመግባት ያቀበለቻትን ኳስ ዳግማዊት ሰለሞን ሞክራ ከደ ውጪ በመወጣው አጋጣሚ የተጀመረው ጨዋታ በመከላከያ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ቀጥሎ በ24ኛው ደቂቃ የመጀመርያው ጎል ተስተናግዷል። ሔለን እሸቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች በተዘናጉበት ሰዓት ያገኘችውን ዕድል ተጠቅማ በማስቆጠር ጦሩን መሪ አድርጋለች።
ከጎሉ በኋላም የበላይነት ይዘው የቀጠሉት መከላከያዎች በጊዮርጊስ ተከላካዮች ብዙም ክፍተት ባለማግኘታቸው ከርቀት ኢላማቸውን ያልጠበቁ የጎል ሙከራዎች ለማድረግ ተገደዋል። በዚህም በ38ኛው ደቂቃ የምስራች ላቀው ከርቀት አክርራ በመምታት አስቆጥራ ልዩነቱን ወደ ሦስት አስፍታለች። በ41ኛው ደቂቃም በጨዋታው ድንቅ የነበረችው አረጋሽ ከልሳ በተመሳሳይ አከረርራ ከርቀት የመታችው ኳስ የግቡ አግዴሚን ለትሞ ሲመለስ ብሩክታዊት አግኝታ ያመከነችውም ሌላ የጎል እድል ነበር።
የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ለረጅም ደቂቃዎች በመሐል ሜዳ ኳስ ሲንሸራሸር የቆየ ሲሆን መከላከያዎች በአረጋሽ፣ ሲሳየ እና የምስራች አማካኝነት ከርቀት ከሚያደርጓቸው ሙከራዎች በቀርም እስከ መጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች ድረስ የረባ እንቅስቃሴ አልታየም። በ82ኛው ደቂቃ ፋና ዘነበ ከግራ መስመር አክርራ በመምታት ለጥቂት የወጣባት ኳስ ጊዮርጊስን ወደ ጨዋታው ለመመለስ የተቃረበች ሙከራ ነበረች።
ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ የቀኝ መስመር ተከላካይዋ ምህረት መለሰ በጥሩ ሁኔታ ወደ ፊት በመጓዝ ያሻገረችው ኳስ አቅጣጫ ቀይሮ በግሩም ሁኔታ ወደገግብነት በመለወጥ መከላከያ 3-0 እንዲመራ አስችላለች። ከዚህ ጎል በኋላም ተቀይረ የገባችው ሔለን ሰይፉ ከቀኝ የሳጥኑ ክፍል አክርራ ግብ ጠባቂዋ ያዳነችበች እንዲሁም ለመዲና አወል አመቻችታላት መዲና የሞከረችውን ግብ ጠባቂዋ ብዙዓየሁ የመለሰችው ተጨማሪ ጎል ሊሆኑ የሚችሉ ሙከራዎች ነበሩ።
በክልል ከተሞች…
ድሬዳዋ ከተማ በሜዳው አዲስ አበባ ከተማን አስተናግዶ 2-1 አሸንፏል። ዘንድሮ ክስተት የሆነችው አይዳ ዑስማን ሁለቱንም የድሬዳዋ ጎሎች ስታስቆጥር ፍቅርተ ብርሀኑ የአዲስ አበባ ከተማን ብቸኛ ጎል በቅጣት ምት አስቆጥራለች። አይዳ ዑስማን ዛሬ ሁለት ጎሎችን ማስቆጠሯን ተከትሎ የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነቱን በ9 ጎሎች መምራት ችላለች።
አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ 1-1 ተጠናቋል። ሰርካለም ባሳ በ55ኛው ደቂቃ ባስቆጠረችው ጎል አርባምንጭን ቀዳሚ ብታደርግም ነፃነት መና በ71ኛው ደቂቃ ሀዋሳን አቻ አድርጋለች።
ባህርዳር ላይ ጥረት ኮርፖሬት ከ ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ጋር በተመሳሳይ 1-1 ተለያይተዋል። ጤናዬ ለታሞ በ28ኛው ደቂቃ ጥሩነሽ ዲባባን መሪ ስታደርግ አዲስ ንጉሴ በ70ኛው ደቂቃ ለጥረት የአቻነቱን ጎል አስቆጥራለች።
በዘጠነኛው ሳምንት ቀሪ መርሐ ግብር ቀጣይ ማክሰኞ ዲላ ላይ ጌዴኦ ዲላ ከ ኤሌክትሪክ ይጫወታሉ።