ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ስሑል ሽረ ከ ድሬዳዋ ከተማ

ነገ ከሚጀምሩት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ውስጥ ስሑል ሽረ እና ድሬዳዋ ከተማን የሚያገነኛውን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

በሁለት ነጥቦች ልዩነት በታችኛው የሰንጠረዡ ክፍል የተቀመጡት ስሑል ሽረ እና ድሬዳዋ ከተማ ነገ 09፡00 ላይ ደካማ ጉዟቸውን ለማስተካከል ይገናኛሉ። እስካሁን አንድም ድል ያላጣጣሙት ስሑል ሽረዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለት ግቦች ያስቆጠሩበት የመከላከያው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ውጤቱ ለሽረ ለሰባተኛ ጊዜ ነጥብ የተጋራበት ሆኖ ያለፈም ነበር። ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ 11ኛው ሳምንት በሜዳቸው በቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 ተሸንፈዋል። ባህር ዳርን ከረቱበት ጨዋታ በመቀጠል ሁለት ተከታታይ ሽንፈት ያስተናገዱ መሆኑን ተከትሎም ወደ 11ኝነት ወርደዋል። ከነገው ጨዋታ የሚገኙት ነጥቦች ክለቦቹን በመጠኑም ቢሆን ከአደጋው ዞን ከፍ የማድረግ አቅም ያላቸው በመሆኑ ቡድኖቹ ጥሩ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

ስሑል ሽረ እንደሰሞኑ ሁሉ ነገም ሸዊት ዮሃንስ ፣ ሰለሞን ገብረመድህን ፣ መብራህቶም ፍስሃ እና ንስሃ ታፈሰን ከጉዳት ባለማገገማቸው ሳቢያ በነገው ጨዋታ የማይጠቀምባቸው ሲሆን በድሬዳዋ ከተማ በኩል ግን  የረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ ከሚገኘው ራምኬል ሎክ ውጪ ቀሪው የቡድኑ ስብስብ ከጉዳት እና ቅጣት ነፃ ነው።

ከአጥቂ ክፍሉ ግቦችን ማግኘት የከበደው ሽረ የሚፈጥራቸውም የግብ ዕድሎች በርካታ ናቸው ለማለት አያስደፍርም። የሚገኙትንም ጥቂት ዕድሎች ወደ ግብነት ለመቀየር ግን ከፊት መስመር ተሰላፊዎቹ ባለፈ ከሌሎች የቡድኑ አባላትም ጥረትን ይጠይቃል። በነገውም ጨዋታ ቡድኑ ኳስ ተቆጣጥሮ በመጫወት ወደ ግብ ለመድረስ እንደሚጥር ቢታሰብም የማጥቃት ሂደት ላይ ሲሆን የሚሳተፉ ተጫዋቾችን ቁጥር በመጨመር በተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ የተሻለ ጫና መፍጠር ይጠበቅበታል። ለክፉ የማይሰጥ የመከላከል ሪከርድ ያለው ድሬዳዋ ከተማም እንደተጋጣሚው ሁሉ ተለዋዋጭ ከሆነው የአጥቂ ጥምረቱ በቂ ግቦች እያገኘ አይደለም። ነገም በሁለቱ መስመሮቹ በኩል እና ከአማካይ ክፍሉ ጀርባ ክፍተቶችን በመዝጋት በፍጥነት ለፊት አጥቂዎቹ ኳሶችን የማድረስ ዕቅድ እንደሚኖረው ይታመናል። በዚህ ሂደት ውስጥ የመስመር አማካዮቹ ከመከላከል ኃላፊነታቸው ባለፈ ወደ ፊት ገፍተው ተሻጋሪ ኳሶችን ማድረስም ሆነ የግብ ሙከራዎችን የማድረግ ኃላፊነት ሊኖራቸው እንደሚችልም ይታሰባል።
 

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ተጋጣሚዎች በሊጉ የመጀመሪያ የእርስ በርስ ግንኙነታቸውን ያደርጋሉ።

– ስሑል ሽረ በሜዳው ያደረጋቸውን ስድስት ጨዋታዎች በሙሉ በአቻ ውጤት አጠናቋል። ከነዚህ ውስጥ አራቱ ያለግብ የተጠናቀቁ ነበሩ። 

– እስካሁን ከሜዳው ውጪ ድል ያልቀናው ድሬዳዋ ከተማ ከአራት ጨዋታዎች ሁለት የአቻ ውጤቶችን ብቻ ይዞ ተመልሷል።

ዳኛ

–  እስካሁን በዳኘባቸው ሁለት የአንደኛ እና ሰባተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሰባት የቢጫ ካርዶችን የመዘዘው ሳህሉ ይርጋ ይህን ጨዋታ ለመምራት ተመድቧል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ስሑል ሽረ (4-2-3-1)

ሰንደይ ሮቲሚ

አብዱሰላም አማን – ዘላለም በረከት  – ዲሜጥሮስ ወልደስላሴ – ክብሮም ብርሀነ

ሳሙኤል ተስፋዬ – ኄኖክ ካሳሁን

ኪዳኔ አሰፋ – ጅላሎ ሻፊ – ልደቱ ለማ

           
ኢብራሒማ ፎፋና

ድሬዳዋ ከተማ (4-4-2)

ሳምሶን አሰፋ

ገናናው ረጋሳ – አንተነህ ተስፋዬ – ፍቃዱ ደነቀ – ሳሙኤል ዮሃንስ

ሚኪያስ ግርማ – ፍሬድ ሙሺንዲ –  ምንያህል ይመር – ረመዳን ናስር

ሐብታሙ ወልዴ – ኃይሌ እሸቱ

                                                            

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *