በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ያለ አሰልጣኙ ድሬዳዋ ከተማን በሜዳው ያስተናገደው ስሑል ሽረ በሜዳው ለተከታታይ ሰባተኛ ጊዜ የአቻ ውጤት አስመዝግቧል፡፡
ትላንት ዋና አሰልጣኙ ዳንኤል ፀሐዬን እና ረዳት አሰልጣኙን በረከትን ጨምሮ የቡድን መሪው ኤፍሬም ሓዱሽን ቡድኑ እያስመዘገበ ባለው ደካማ ውጤት የተነሳ ደጋፊዎች ባነሱት ተቃውሞ በጊዜያዊነት በማንሳት በቴክኒክ ዳይሬክተሩ ገብረኪሮስ አማረ እየተመራ ወደ ሜዳ የገባው ስሑል ሽረ አዲስ አበባ ላይ ከመከላከያ አቻ ከወጡበት ስብስብ ሁለት ተጫዋቾችን በማሳረፍ ኄኖክ ካሳሁን እና አሸናፊ እንዳለን በደሳለኝ ደባሽ እና ሰዒድ ሁሴን ሲተኩ በቅዱስ ጊዮርጊስ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ግብ ተቆጥሮበት በሜዳው ሽንፈት የገጠመው ድሬዳዋ ከተማ በኃይሌ እሸቱ ምትክ ዘነበ ከበደን ብቻ በመለወጥ የዛሬውን ጨዋታ ጀምሯል፡፡
በስራ ቀን እንደመደረጉ እጅግ አነስተኛ የተመልካች ቁጥር የታየበትና ፌድራል ዳኛ ሳህሉ ይርጋ በጥሩ ዳኝነት የመራው ጨዋታ ለተመልካች የማይማርክ፣ መሐል ሜዳ ላይ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የተገደበ፣ ከሙከራዎች ይልቅም የሚቆራረጡ ኳሶች የበዙበት ሆኖ ታይቷል፡፡ ስሑል ሽረዎች በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች በኳስ ቁጥጥር ተሽለው ቢታዩም ወደ ፊት በመውጣት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ሲደርሱ ጠጣር የመከላከል መንገድን ሲከተሉ በነበሩት የድሬዳዋ ተከላካዮች ሲነጠቁ በተደጋጋሚ ተስተውሏል፡፡ በአንፃሩ ድሬዳዋ ከተማ መከላከልን መሰረት አድርገው ከስሑል ሽረ ተጫዋቾች የሚላኩትን ረጃጅም ኳሶች ከማምከን እና ተደራጅተው ከመከላከል ውጪ ወደ ስሑል ሽረ የግብ ክልል መድረስ ያልቻሉበት ነበር።
ከእረፍት መልስ ድሬዳዋ ከተማዎች ከመጀመሪያው በተሻለ መልኩ ግብ ለማስቆጠር በተለይ በአጥቂ ሐብታሙ ወልዴ አማካኝነት መጫወት ቢችሉም የመጨረሻዎቹ ኳሶች ግን ፍሬያማ ሲሆኑ አልታየም ። በስሑል ሽረ በኩል በ80ኛው ደቂቃ ከመልሶ ማጥቃት የተገኘችን ኳስ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ሚዲ ፎፋና ከማዕዘን ምት መምቻ ጠርዝ ላይ ሲሻገርለት በደረቱ አውርዶ መሬት ለመሬት አክርሮ ወደ ግብ ቢመታም የድሬዳዋ ከተማ ግብ ጠባቂ ሳምሶን አሰፋ አድኖበታል። ሙከራዋም በ90 ደቂቃው የጨዋታ እንቅስቃሴ ጠንካራ ልትባል የምትችል ብቸኛ ሙከራ ነበረች ማለት ይቻላል።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ድሬዳዋ ከተማዎች አጥቅተው ሲጫወቱ በአንፃሩ ስሑል ሽረ ወደ ኋላ በማፈግፈግ የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎችን መከላከል ምርጫቸው አድርግዋል። ጨዋታውም ከነበረው ደካማ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ አንፃር ተገቢ ሊባል በሚችል ውጤት ያለ ግብ ተጠናቋል፡፡
ውጤቱን ተከትሎ በሊጉ እስካሁን ድል ማስመዝገብ ያልቻለ ብቸኛው ቡድን የሆነው ስሑል ሽረ ከ11 ጨዋታዎች በአስገራሚ ሁኔታ ስምንት አቻዎች በማስመዝገብ በ9 ነጥቦች 13ኘሐ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ደረሬዳዋ ከተማ ከ10 ጨዋታ በ10 ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።