ዛሬ የጀመረው የሊጉ 12ኛ ሳምንት ነገ ሲቀጥል ሀዋሳ ከተማ እና ደቡብ ፖሊስ በሚገናኙበት ጨዋታ ዙሪያ ተከታዩን ዳሰሳ አዘጋጅተናል።
የሀዋሳው ሰው ሰራሽ ሜዳ ነገ 09፡00 ላይ ሰሞኑን ከድል የራቀው ሀዋሳ ከተማን እና በአስቸጋሪ ጉዞው የቀጠለው ደቡብ ፖሊስን ያገናኛል። ከሳምንታት በፊት ሊጉን ይመሩ የነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች በመቐለ እና ኢትዮጵያ ቡና የደረሰባቸው ሽንፈት ወደ አምስተኛነት ገፍቷቸው ይገኛሉ። ይሁን እንጂ በንፅፅር ቀለል ካለው የነገ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማሳካት ከቻሉ ከሊጉ መሪ ጋር ያላቸውን ልዩነት በማጥበብ ራሳቸውን በፉክክሩ ውስጥ ለማቆየት ይችላሉ። ሣምንት በሌላኛው የከተማው ክለብ ሲዳማ ቡና ሽንፈት የደረሰበት ደቡብ ፖሊስ አሁንም ከ15ኛ ደረጃ ከፍ ማለት አልቻለም። ክለቡ ምንም ተስተካካይ ጨዋታ የሌለው መሆኑ ሲታሰብ ደግሞ ያለበት ሁኔታ አስጊ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። ሆኖም ፖሊስ ምን አልባት ከነገው ጨዋታ ውጤት ካገኘ መጠነኛ ተስፋ ሊፈነጥቅ ይችላል።
በጨዋታው ሀዋሳ ከተማ ያለምንም ጉዳት እና ቅጣት ሙሉ ስብስቡን ይዞ ይቀርባል። ቡድኑ ከኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ በተለየም እንደቀድሞው ሁሉ በሦስት የኋላ ተከላካዮች የሚጀምር አሰላለፍን እንደሚጠቀም ይጠበቃል። በደቡብ ፖሊስ በኩል ደግሞ በሲዳማው ጨዋታ ከረጅም ጊዜ ጉዳት በኋላ ተመልሶ የመሰለፍ ዕድል አግኝቶ የነበረው እና በድጋሚ ጉዳት ያስተናገደው ብርሀኑ በቀለ እንዲኩን ቢኒያም አድማሱ በጉዳት እንደማይሰለፉ ታውቋል።
የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– ሁለቱ ቡድኖች በ2001 እና 2002 የውድድር ዓመታት ከተጋናኙባቸው አራት ጨዋታዎች ሦስቱን በአቻ ውጤት ሲያጠናቅቁ ሀዋሳ በመጨረሻው ግንኙነታቸው የ 2-0 አሸናፊ ሆኗል። ሀዋሳ ከተማ አራት ደቡብ ፖሊስ ደግሞ ሁለት ግቤችን አስቆጥረዋል።
– ሀዋሳ ላይ ክለቦቹ እስካሁን ባደረጓቸው ጨዋታዎች ሀዋሳ ከተማ በሲዳማ እና መቐለ ብቻ ሽንፈት የቀመሰ ሲሆን ደቡብ ፖሊስ ደግሞ በብቸኛው የዓመቱ ድሉ ደደቢትን አሸንፏል። ከዚህ ውጪ ደበብ ፖሊስ አምስቱን ጨዋታዎች በሽንፈት ሲደመድም ሀዋሳ በተቃራኒው አምስት ድሎችን አጣጥሟል።
ዳኛ
– በአራተኛ እና ስምንተኛ ሳምንታት በዳኘባቸው ሁለት ጨዋታዎች ስድስት የቢጫ እና አንድ የቀይ ካርዶች የመዘዘው እያሱ ፈንቴ ይህን ጨዋታ ለመምራት ተመድቧል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ሀዋሳ ከተማ (3-4-1-2)
ሶሆሆ ሜንሳህ
አዲስዓለም ተስፋዬ – ላውረንስ ላርቴ – መሣይ ጳውሎስ
ዳንኤል ደርቤ –ኄኖክ ድልቢ– ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን – ያኦ ኦሊቨር
ታፈሰ ሰለሞን
አዳነ ግርማ – እስራኤል እሸቱ
ደቡብ ፖሊስ (4-3-3)
ዳዊት አሰፋ
አናጋው ባደግ – ደስታ ጊቻሞ – አዳሙ መሀመድ – አበባው ቡታቆ
አዲስአለም ደበበ – ኤርሚያስ በላይ – ዘላለም ኢሳያስ
ብሩክ ኤልያስ – በኃይሉ ወገኔ – ኄኖክ አየለ