የመጨረሻው የዛሬ ቅድመ ዳሰሳችን ትኩረት የአማራ ደርቢ ይሆናል።
በባህር ዳር ኢንተርናሽናል ስታድየም ባህር ዳር ከተማ እና ፋሲል ከነማን የሚያገናኘው የአማራ ደርቢ ነገ 09፡00 ላይ ይከናወናል። ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው ዘንድሮ ወደ ሊጉ ብቅ ያሉት ባለሜዳዎቹ ባህርዳሮች ከስምንተኛው ሳምንት በኋላ መቀዛቀዝ እየታየባቸው ይገኛል። ሳምንት በወልዋሎ የተሸነፉበትን ጨዋታ ጨምሮ የጣሏቸው ሰባት ነጥቦችም ወደ ዘጠነኛነት ዝቅ አድርጓቸዋል። ሆኖም ነገ ማሸነፍ ከቻሉ እስከ አምስተኝነት ከፍ ማለት ሲችሉ ያሏቸው ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች ደግሞ ይበልጥ የመሻሻል ዕድልን ይሰጧቸዋል። አራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ፋሲል ከተማም እንደተጋጣሚው ሁሉ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች ያሉት ሲሆን በሊጉ አናት የመቀመጥ ተስፋውም እንዳለ ነው። ሆኖም ያ እንዲሆን በመደበኛዎቹ መርሐ ግብሮችም ውጤቱን ማሳመር ይጠበቅበታል። ፋሲል በሜዳው ደደቢት እና ወላይታ ድቻን በመርታት ሲሆን ነገ ባህር ዳርን የሚገጥመው በጨዋታው ሦስተኛ ተከታታይ የሉግ ድል የማስመዝገብ አላማም ይኖረዋል።
በ10ኛው ሳምንት ጉዳት ያጋጠመው ዳንኤል ኃይሉ ሳምንት ባህር ዳር ከተማ ወደ መቐለ አምርቶ በወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ ሽንፈት ካስተናገደበት ጨዋታ ውጪ የነበረ ሲሆን ተጨዋቹ አሁንም ከጉዳቱ ባለማገገሙ በነገው ስብስብ ውጥም አልተካተተም። ባህር ዳሮች ከዳንኤል ውጪ ምንም አይነት የጉዳትም ሆነ የቅጣትም ዜና የለባቸውም። በርከት ያሉ ተጫዋቾቹ ጉዳት ላይ የሚገኙት ፋሲል ከነማ ሙጂብ ቃሲም ፣ ያስር ሙገርዋ ፣ ኢዙ አዙካ ፣ ኤፍሬም አለሙ እና ፋሲል አስማማውን በጉዳት ምክንያት አጥቷል።
የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– ሁለቱ ክለቦች በፕሪምየር ሊጉ የመጀመሪያ የእርስ በርስ ግንኙነታቸውን የሚያደርጉ ሲሆን በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የተገናኙበት ጨዋታ በባህርዳር ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቆ ነበር።
– ባህር ዳር ከተማ ሜዳው ላይ ካስተናገዳቸው አራት ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፎ በሁለቱ ነጥብ ተጋርቷል።
– ፋሲል ከነማ ከሜዳው በወጣበት የመጀመሪያ ጨዋታ ከተሸነፈ በኋላ ሁለት ጊዜ አሸንፎ ሲመለስ አንዴ አቻ ተለያይቷል።
ዳኛ
– ጨዋታው በማኑሄ ወልደፃዲቅ የመሀል ዳኝነት ይከናወናል። አርቢትሩ በዚህ ዓመት ሁለት ጨዋታዎችን ያዳኘ ሲሆን ዘጠኝ የማስጠንቀቂያ ካርዶች የመዘዘ ሲሆን አንድ የፍፁም ቅጣት ምትም ሰጥቷል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ባህርዳር ከተማ (4-3-3)
ሐሪሰን ሄሱ
ሣለአምላክ ተገኝ – ወንድሜነህ ደረጄ – አቤል ውዱ – አስናቀ ሞገስ
ደረጄ መንግስቱ – ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – ኤልያስ አህመድ
ወሰኑ ዓሊ – ጃኮ አራፋት – ግርማ ዲሳሳ
ፋሲል ከነማ (4-3-3)
ሚኬል ሳማኬ
ሰዒድ ሁሴን – ያሬድ ባየህ – ከድር ኩሊባሊ – አምሳሉ ጥላሁን
ዮሴፍ ዳሙዬ – ሐብታሙ ተከስተ – ሱራፌል ዳኛቸው
ሽመክት ጉግሳ – ኤዲ ቤንጃሚን – አብዱራህማን ሙባረክ