በ12ኛው ሳምንት የሊጉ የመጨረሻ ጨዋታ ደደቢትን ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሳላዲን ሰዒድ እና አቤል ያለው ግቦች 2-0 አሸንፏል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ድሬዳዋ ከተማን ካሸነፈበት ጨዋታ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ አቡበከር ሳኒን በበኃይሉ አሰፋ የተካ ሲሆን በደደቢቶች በኩል ደግሞ ከአዳማ ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ የሁለት ተጫዋቾች ቅያሪ አድረዋል። ቢዚህም እንዳለ ከበደ እና አሌክሳንደር ዐወት በተጠባባቂነት ጨዋታውን ሲጀምሩ በምትካቸው አቤል እንዳለ እና አክዌር ቻሞ በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ተካተዋል።
ብዙም ሳቢ ያልሆነ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ ደደቢቶች ኳስ ይዘው በአጫጭር ቅብብሎች ለማጥቃት ባለመ መልኩ ቢጀምሩም የሜዳውን አጋማሽ ማለፍ ከብዷቸው ታይቷል። ሙከራ በማድረግ ቀዳሚ መሆን የቻሉትም ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሲሆኑ 4ኛው ደቂቃ ላይ ኄኖክ አዱኛ ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ ያሻማውን ኳስ በኃይሉ አሰፋ ሳጥን ውስጥ አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ በቀጠለው ጨዋታ ደደቢቶች ኳስ ለመያዝ ጥረታቸውን ቢቀጥሉም በቀላሉ ጫና ውስጥ እየገቡ በተደጋጋሚ መረጋጋት ሲሳናቸው እና ቅብብሎቻቸው እየተበላሹባቸው ለመነጠቅ ሲገደዱ ይታይ ነበር። ያም ቢሆን 16ኛው ደቂቃ ላይ ሳላዲን በርጌቾን በጉዳት አጥተው ከረጅም ሳምንታት በኋላ በተመለሰው ምንተስኔት አዳነ ለመተካት የተገደዱት ቅዱስ ጊዮርጊሶችም ከሚያቋርጡት ኳስ ሙከራዎችን ለማድረግ ጊዜ ወስዶባቸዋል።
ጊዮርጊሶች በሚያሳድሩት ጫና የደደቢቶችን ስህተት ተከትሎ ወደ ሳጥን መግባት የጀመሩት 18ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። በዚህም በኃይሉ ከግራ ያሻማው ኳስ ወደ ግብ አምርቶ ረሽድ ማታውሲ ጥረት ሊድን ችሏል። ከደቂቃ በኋላ ደግሞ ጌታነህ ከበደ ከናትናኤል ዘለቀ በተላከለት ኳስ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ሲስት ናትናኤልም 19ኛው ደቂቃ ላይ ተመሳሳይ አጋጣሚ ቢገናኝም ሙከራው ወደ ውጪ ወጥቷል። በጥቂት ቅፅበቶች መሀል ሜዳውን በተሻገሩት ደደቢቶች በኩል ግን የታየው ብቸኛ ሙከራ 24ኛው ደቂቃ ላይ ዓለምአንተ ካሳ ከሳጥን ውጪ በቀጥታ የመታው የቅጣት ምት በፓትሪክ ማታሲ ጥረት ሲመክን ነበር።
በሂደት ደደቢቶች ከመጀመሪያው የተሻለ ቀጥተኝነት እየታየባቸው ወደ አኩዌር ቻሞ የሚልኳቸው ኳሶች መታየት በጀመሩባቸው ደቂቃዎች ላይ ግብ አስተናግደዋል። 27ኛው ደቂቃ ላይ ሳላዲን ሰዒድ በግምት ከ30 ሜትር ርቀት ቀጥታ የመታው ቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ ከመረበረ አርፎ ቅዱስ ጊዮርጊስን መሪ አድርጓል። ጊዮርጊሶች ከግቡ በኋላ በተከተሉት ደቂቃዎች ተነቃቅተው ቢታዩም ደደቢቶች ቀስ በቀስ ጨዋታ ወደ ጊዮርጊስ ሜዳ እንዲያመዝን ማድረግ ችለዋል። ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል የደረሱባቸው ጊዜያት ቢኖሩም የግራ መስመር ተከላካዩ መድኃኔ ብርኃኔ አሻምቶለት አኩዌር በግንባር ለመሞከር ጥረት አድርጎ ሳይደርስበት ከቀረው ኳስ ውጪ የተሻለ አጋጣሚ አልፈጠሩም። ጊዮርጊሶችም አልፎ አልፎ ተሻጋሪ ኳሶችን ወደ ፊት ከመጣል ውጪ ንፁህ የግብ ዕድል ሳይፈጥሩ አጋማሹ ተጠናቋል።
ሁለተኛው አጋማሽ በጀመረባቸው ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች የቆመ ኳስ ዕድሎችን ማግኘት ቢችሉም አስደንጋጭ ሙከራዎች ግን አልታዩም ነበር። ከኳስ ውጪ ወደ ኋላ ማፈግፈግን ምርጫቸው ያደረጉት ደደቢቶች ኳስ ሲይዙ መስርተው ለመውጣት ፍላጎት ቢያሳዩም እንደመጀመሪያው ሁሉ ቅብብሎቻቸው ዘላቂ መሆን ተስኗቸዋል። በፈጣን ሽግግር ወደ ደደቢት የግብ ክልል ይደርሱ የነበሩት ጊዮርጊሶች በበኩላቸው በበኃይሉ እና ኄኖክ በኩል ወደ ውስጥ ኳሶችን ቢያሻግሩም ሁለቱ የፊት አጥቂዎቻቸው ዕድሉን ከመጠቀማቸው በፊት በደደቢት ተከላካዮች ይቀደሙ ነበር።
አኩዌር ቻሞን እና ዳግማዊ አባይን በአሌክሳንደር ዐወት እና እንዳለ ከበደ የቀየሩት ደደቢቶች በለውጦቹ ከባድ ሙከራዎችን ማድረግ ባይችሉም የተሻለ የኳስ ፍሰት ኗሯቸው ነበር። 70ኛው ደቂቃ ላይ አሌክሳንደር ከዓለምአንተ ተቀብሎ ሳጥን ውስጥ ሊሞክር ሲል አስቻለው ቀድሞ ያወጣበት የቡድኑ የተሻለ አጋጣሚ ነበር። 63ኛው ደቂቃ ላይ ሳላዲን ከማዕዘን በተሻገረ ኳስ ካደረገው የግንባር ሙከራ በኋላ ሌላ ዕድል ያልፈጠሩት ጊዮርጊሶች ያደረጉት ቅያሪ ግን ፍሪያማ አድርጓቸዋል። 71ኛው ደቂቃ ላይ በጌታነህ ከበደ ተቀይሮ የገባው አቤል ያለው ሁለተኛውን ግብ ለማስቆጠር አንድ ደቂቃ ብቻ ነበር ያስፈለገው። ሙሉዓለም መስፍን ከአቤል እንዳለ የነጠቀውን ኳስ ከደደቢቱ መሀል ተከላካይ ዳዊት ጀርባ ሲጥልለት ፈጣኑ አጥቂ ኳሷን በግብ ጠባቂው አናት ላይ በመላክ በቀድሞው ክለቡ ላይ ሁለተኛዋን ግብ አስቆጥሯል።
መሪነታቸውን ያሰፉት ጊዮርጊሶች የአቤልን ፍጥነት በመጠቀም ከተከላካይ ጀርባ በሚጥሏቸው ኳሶች ይበልጥ አስፈሪ ሆነው ሲቀጥሉ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ የነበራቸው ደደቢቶችም ክፍተቶችን ፍለጋ በጊዮርጊስ ሜዳ ላይ ኳስ ይዘው መቆየት ችለው ነበር። ሆኖም ጨዋታው የውጤት ለውጥ ሳይታይበት የተጠናቀቀ ሲሆን ጊዮርጊሶች 86ኛው ደቂቃ ላይ ኄኖክ ካሻማው እና ሳላዲን በግንባር ከሞከረው እንዲሁም 89ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉዓለም ሳጥን ውስጥ አንድ ተጫዎች አሸማቆ አክርሮ በመታው ኳስ ሙከራዎችን ቢያደርጉም የመጀመሪያው በማታውሲ ሁለተኛው ደግሞ በዳዊት ጥረት ግብ ከመሆን ድነዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከጨዋታው ባገኛቸው ነጥቦች ወደ ሁለተኝነት ሲመለስ ደደቢት በነበረበት የመጨረሻ ደረጃ ላይ ለመቅረት ተገዷል።