በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ወላይታ ድቻን ያስተናገደው ጅማ አባ ጅፋር 2-0 በማሸነፍ በውድድር በዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ በሜዳው ሙሉ ሶስት ነጥብ አግኝቷል።
ጅማ አባጅፋር ባሳለፍነው ሳምንት በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ወደ ሞሮኮ አቅንቶ በሃሳኒያ አጋዲር ከተሸፈነው ስብስብ ውስጥ ከድር ኸይረዲንን በመላኩ ወልዴ፣ ማማዱ ሲዲቤን በኤርሚያስ ኃይሉ፣ ዲዲዬ ለብሪን በአስቻለው ግርማ በመተካት በ4-3-3 አሰላለፍ ወደ ሜዳ ሲገባ ወላይታ ድቻዎች ደግሞ ባሳለፍነው ሳምንት በፋሲል ከተማ ከተሸነፈው ቡድናቸው እዮብ ዓለማየሁን በውብሸት ክፍሌ፣ ፍፁም ተፈሪን በዘላለም ኢያሱ ቀይረው በ 4-1-3-2 አሰላለፍ የዛሬውን ጨዋታ ጀምረዋል።
ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ በጥሩ ብቃት የመሩት ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ፈጣን እንቅስቃሴ ታይቶበታል። በአራተኛው ደቂቃ መስዑድ መሐመድ በቀኝ መስመር የድቻን ተጫዋቾች አታሎ በማለፍ ለአስቻለው ግርማ ሲያቀብለው ጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው አስቻለው ወደግብ ሞክሮ ታሪክ ጌትነት እንደምንም ያወጣበት አስደንጋጭ ሙከራ ነበር።
ከዚህ ሙከራ በኋላ ጨዋታው ላይ መጠነኛ መቀዛቀዝ ሲታይበት በቀጣይ ሰላሳ ደቂቃዎችም በኳስ ቁጥጥር ረገድ ወላይታ ድቻዎች ፍፁም ብልጫ ነበራቸው። የቸርነት ጉግሳ እና በረከት ወልዴ የመሐል ሜዳ እንቅስቃሴ ወላይታ ድቻ ጨዋታውን እንዲቆጣጠር እና ጅማዎችም ኳስን መልሶ ለማግኘት እንዲከብዳቸው ትልቅ ሚና ነበረው። በተለይም በግራ መስመር የሚጫወተው ቸርነት ጉግሳ በተደጋጋሚ የጅማ ተከላካዮችን ሲረብሽ አርፍዷል። በ 27ኛው ደቂቃ ቸርነት ከውብሸት ክፍሌ ጋር በአንድ ሁለት ቅብብል ተጫውቶ የጅማ ተከላካዮችን ካለፈ በኋላ ከዳንኤል አጃዬ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ በግቡ አናት ላይ የሰደደው ኳስ የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር።
የወላይታ ድቻ ጫና ሲቀጥል ከበረከት ወልዴ ከመሀል ሜዳ ወደ ግራና ቀኝ የሚሰራጩ ኳሶች ዲቻዎች በቀላሉ ወደ ጅማ ግብ ክልል ለመድረስ ቢችሉም ከክንፍ ወደ መሐል ተመልሰው የሚሻገሩ ኳሶች ግን አጥቂው ባዬ ገዛኸኝ በጅማ ተከላካዮች ቁመት በመዋጡ ፍሬያማ መሆን ተስኗቸው ታይቷል። በ31ኛው ደቂቃም በረከት ወልዴ ለሳምሶን ቆልቻ ያሻገረውን ኳስ ሳምሶን በግንባሩ ሞክሮት የግቡን ቋሚ ታኮ የወጣው አጋጣሚ ግብ ባለመሆኑ ድቻዎችን ዕድለ-ቢስ አድርጓቸዋል።
ባለሜዳዎቹ በጨዋታ በመበለጣቸው እና አጥቂው ቢስማርክ አፒያ ያሳየው አቋም ደካማ ነው በሚል የጅማ አባጅፋር ደጋፊዎች ተቋውሞ ሲያሰሙም ተስተውሏል። ጅማዎች በመሀል ሜዳ በተወሰደባቸው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ምክንያትም ከተከላካዮች በቀጥታ ለአጥቂዎች በሚሻገሩ ረጃጅም ኳሶች ወደግብ ለመቅረብ ሙከራ ለማድረግ ተገድደው ነበር። በ38ኛው ደቂቃ አስቻለው ግርማ ከኋላ በረጅሙ የተጣለለትን ኳስ ይዞ በሚገባበት ወቅት በድቻ ሳጥን ውስጥ ጥፋት ስለተሰራበት የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ አስቻለው አስቆጥሮ ጅማን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከግቡ መቆጠር በኋላ የድቻዎች ተነሳሽነት ወርዶ ሲታይ ጅማዎች በአንፃሩ የተሻለ ተንቀሳቅሰዋል። በ41ኛው ደቂቃ መስዑድ በቀኝ የሳጥን ጠርዝ አታሎ ገብቶ ከግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነት ፊት ለፊት ለነበረው ኤርሚያስ ቢሰጠውም ኤርሚያስ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ሁለተኛው አጋማሽ በጨዋታም ሆነ በግብ ሙከራ ረገድ ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ነበር። አጋማሹን ኤርሚያስን በዲዲዬ ለብሪ ቀይረው የጀመሩት ጅማዎች ከእረፍት በፊት የነበረባቸውን ክፍተት በማረም ብልጫ ወስደው መጫወት ችለዋል። ድቻዎች በአንፃሩ ወደ ኃላ በማፈግፈግ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት የመረጡ ይመስል ነበር። ተቀይሮ የገባው ዲዲዬ ለብሬ በቀኝ መስመር እንዲሁም አስቻለው በግራ የሚያደርጉት እንቅስቃሴም ይበልጥ ዲቻዎችን ወደ ኋላ እንዲሳቡ ያስገደደ ነበር። በ52ኛው ደቂቃ አስቻለው በግራ መስመር ከመስዑድ የተሰጠውን ኳስ ከታሪክ ጌትነት ፊት-ለፊት ተገናቶ ያመከነው አጋጣሚ ጥሩ የግብ ማግባት እድል ነበር።
ድቻዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተቃራኒው በመልሶ ማጥቃት ወደ ግብ ለመድረስ ሞክረዋል። ተቀይሮ የገባው አንዱዓለም ከሳጥን ውጭ የዳንኤል አጄ መውጣት በመመልከት ወደ ግብ የሞከረው ኳስ ዳንኤል እንደምንም ሲያወጣበት በ60ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት በድጋሚ ባዬ ያሻገረለትን ኳስ አንዱዓለም ሞክሮ የግቡን የግራ ቋሚ ታካ ግብ ሳትሆን ቀርታለች፡፡
ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር የደጋፊዎች ጫና የጅማዎች ጫና እየበረታ ሲመጣ የድቻ ተካላካዮች ጫናን መቋቋም ሲሳናቸው እንዲሁም ትኩረት ማጣት ተስተውሎባቸዋል። 73ኛው ደቂቃ ዲዲዬ ለብሪ በዚሁ የተከላካዮች ትኩረት ማጣት ተጠቅሞ ያገኘውን ግልፅ እድል ሲያባክን በድጋሚ በ76ኛው ደቂቃ የተከላካዮችን ስህተት በመጠቀም ማማዱ ሲድቤ ጅማዎች በዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በሜዳቸው ሶስት ነጥብ እንዲጨብጡ ያረጋገጠች ግብ አስቆጥሯል ፡፡
ከግቡ መቆጠር በኋላ ጅማዎች በይበልጥ በነፃት በመጫወት በተደጋጋሚ ከወላይታ ድቻው ግብ ጠባቂ ታሪክ ጌትነት ጋር አንድ ለአንድ እየተገናኙ ያመከናቸው ኳሶች መቆጠር ቢችሉ የግብ ልዩነቱን ይበልጥ ማስፋት የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ። ጨዋታውም በቀሩት ደቂቃዎች ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርበት በጅማ አባ ጅፋር 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።