ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ደቡብ ፖሊስ ከ መቐለ 70 እንደርታ

ደቡብ ፖሊስ እና መቐለ 70 እንደርታ የሚገናኙበትን የ13ኛ ሳምንት ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

በተለያየ የውጤት ጎዳና ላይ የሚገኙት ደቡብ ፖሊስ እና መቐለ 70 እንደርታን የሚያገናኘው የነገው ጨዋታ በ 09፡00 ላይ በሀዋሳው ሰው ሰራሽ ሜዳ ይጀምራል። በአስረኛው ሳምንት ከስሑል ሽረ ጋር ነጥብ ከተጋሩ በኋላ ዳግም ወደ ሽንፈት ጉዞ የገቡት ደቡብ ፖሊሶች በከተማ ተቀናቃኞቻቸው ሲዳማ እና ሀዋሳ ተከታታይ ሽንፈት አስተናግደዋል። በመሆኑም የነበሩበት አምስት ነጥብ ላይ ቆመው 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ሦስት ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሩት መቐለ በአንፃሩ ባሳየው መሻሻል ሰባተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ከመሪው ጋር ያለው ልዩነትም ወደ አምስት ዝቅ ብሏል። መቐለዎች ወድ ውጤት እንዲመለሱ የረዷቸውን የመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎቻቸውን በድል ሲያጠናቅቁ አንድ ግብ ብቻ ነበር የተቆጠረባቸው። ቡድኑ ነገ ውጤት ከቀናውም እስከ አራተኝነት ከፍ የማለት ዕድል ይኖረዋል።

ደቡብ ፖሊስ ከነገው ጨዋታ በፊት ጉዳት ላይ ይገኝ የነበረው ቢኒያም አድማሱ ሲመለስለት በበርካታ ጨዋታዎች የቡድኑን የቀኝ መስመር ጥቃት ይመራ የነበረው ብሩክ ኤልያስ እና ብርሀኑ በቀለ ደግሞ በተቃራኒው በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጪ ሆነዋል። በመቐለ 70 እንደርታ በኩል ባለፈው ሳምንትም በጉዳት ያልተሰለፉት አቼምፖንግ አሞስ ፣ ሳሙኤል ሳሊሶ እና አሸናፊ ሃፍቱ ባለማገገማቸው ከቡድኑ ጋር ወደ ሀዋሳ አለማቅናታቸው ታውቋል።

በጨዋታው ቢያንስ ግብ እስኪቆጠር ክፍት የሆነ እና በማጥቃት ላይ የተመሰረተ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ይጠበቃል። አማካይ ክፍሉ ላይ ተደጋጋሚ ለውጦች እያደረገ የሚገኘው ደቡብ ፖሊስ በተለይም ከግራ መስመር እና ከጥልቅ የመሀል ክፍሉ በሚነሱ ቀጥተኛ ኳሶች ወደ መቐለ ሳጥን ለመግባት እንደሚጥር ይጠበቃል። በቡድኑ ደካማ ጉዞ ውስጥ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ግቦችን በማስቆጠር ተስፋ እያሳየ የሚገኘው ኄኖክ አየለን ጨምሮ የደቡብ ፖሊስ የመስመር ጥቃት የግብ አጋጣሚዎችን የመፍጠር ዕድል ይኖራቸዋል። በመቐለዎች በኩል በጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት በተለይም ከመሀል ሜዳ የሚመነጩ ጥቃቶችን በማቋረጥ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስን ያለመ እንቅስቃሴ ይጠበቃል። ለዚህ አካሄድ የሚመቸው እና ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አንድ አንድ ግቦች ያስቆጠረው አማኑኤል ገብረሚካኤል እንቅስቅቃሴም ተጠባቂ ነው።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ የእርስ በርስ ግንኙነታቸውን ያደርጋሉ።

– ደቡብ ፖሊስ ሀዋሳ ላይ ካደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች በአራቱ ላይ ግብ እያስቆጠረ ቢወጣም ድል የቀናው ግን በአንዱ ብቻ ሲሆን በሌሎቹ ተሸንፏል።

– መቐለ 70 እንደርታ  ከሜዳው ከወጣባቸው አራት ጨዋታዎች በሁለቱ ተሸንፎ በአንዱ አቻ ሲለያይ ነገ የሚጫወትበት ሜዳ ላይ ባደረገው ጨዋታ ሀዋሳ ከተማን ማሸነፍ ችሎ ነበር።

ዳኛ

– ጨዋታው በአምስተኛው ሳምንት የደቡብ ፖሊስ እና ፋሲል ከነማን ጨዋታ ዳኝቶ ሦስት የማስጠንቀቂያ ካርዶችን ለመዘዘው በፀጋው ሽብሩ የዓመቱ ሁለተኛ የሊግ ጨዋታ ይሆናል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ደቡብ ፖሊስ (4-3-3)

ዳዊት አሰፋ

አናጋው ባደግ – ደስታ ጊቻሞ  – አዳሙ መሀመድ – አበባው ቡታቆ

ኤርሚያስ በላይ – ዮናስ በርታ – ዘላለም ኢሳያስ

የተሻ ግዛው  – በኃይሉ ወገኔ – ኄኖክ አየለ

መቐለ 70 እንደርታ (4-2-3-1)

ፊሊፔ ኦቮኖ

ስዩም ተስፋዬ – አሌክስ ተሰማ – አሚኑ ነስሩ – አንተነህ ገብረክርስቶስ

ጋብርኤል አህመድ – ሚካኤል ደስታ

አማኑኤል ገብረሚካኤል – ሐይደር ሸረፋ – ዮናስ ገረመው

ያሬድ ከበደ

Leave a Reply