የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዝዮን አስረኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ መካሄድ ሲጀምሩ ጌዴኦ ዲላ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሜዳቸው ውጪ ድል አስመዝግበዋል።
የአዲስ አበባ ስታድየም ውሎ
08:00 ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ጌዴኦ ዲላን ያገናኘው ጨዋታ በእንግዳው ቡድን 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ጎሎች እና ጥሩ እንቅስቃሴ በታየበት የመጀመርያ አጋማሽ ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ የነበሩት ጊዮርጊሶች ነበሩ። በ12ኛው ደቂቃ መልካም ተፈራ ከሜዳው አጋማሽ ወደ ግብ የላከችው ኳስ የዲላዋ ግብ ጠባቂ ምህረት ተሰማ የትኩረት ችግር ታክሎበት ከመረብ አርፎ ቅዱስ ጊዮርጊስ መሪ መሆን ችሏል።
ጌዴኦ ዲላዎች ለጎሉ በፍጥነት ምላሽ ለመስጠት የተንቀሳቀሱ ሲሆን በ14ኛው ደቂቃ ድንቅነሽ በቀለ ከግራ የሳጥኑ ጠርዝ አክርራ መትታ የግቡ ቋሚ ሲመልስባት በ18ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር በግጉም ሁኔታ ወደ ግብ የላከችው ኳስ ከመረበ አርፎ ዲላን አቻ አድርጋለች።
ከግራ እየተነሳች በማጥቃት ጥሩ ስትንቀሳቀስ የነበረችው ድንቅነሽ በ32ኛው ደቂቃ ላይም በቮሊ የመታችው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶባት በመልስ ምት የተጀመረው ጨዋታ ተመልሶ በዲላዎች እግር ስር ገብቶ አምበሏ ትርሲት መገርሳ ከርቀት አክርራ በመምታት ባስቆጠረችው ጎል ጌዴኦ ዲላን መሪ ማድረግ ችላለች።
በሁለተኛው አጋማሽ ባለሜዳዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊሶች የተሻለ የተንቀሳቀሱ ሲሆን አመዛኙን ክፍለ ጊዜም በዲላ የሜዳ አጋማሽ አሳልፈዋል። ሆኖም የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ስኬታማ ሳይሆን፤ የጎል እድልም ሳይፈጥሩ ቀርተዋል። በ69ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት የተሻማውን ኳስ ወደ ግብነት ቀይረውት የነበረ ቢሆንም ከጨዋታ ውጪ በሚል ሲሻር በ87ኛው ደቂቃ በጥሩ ሒደት ወደ ፊት የሄደውን ኳስ በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረችው ፋና ዘነበ ሳታገኘው የወደቀችበት በጥሩ እድልነቱ የሚጠቀስ ነበር። በመልሶ ማጥቃት እና በረጅሙ ከሚሻገሩ ኳሶች ለመጫወት የሞከሩት ዲላዎች በኩል ደግሞ በ78ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻማው ኳስ ሲመለስ በቅርብ ርቀት የነበረችው ትርሲት መትታ ወደ ውጪ የወጣባት በዚህ አጋማሽ ብቸኛ የሚጠቀስ ሙከራ ነው።
10:00 ላይ የቀጠለው የአዲስ አበባ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ረጃጅም ኳሶች የበዙበት፣ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ እምብዛም ያልታየበት ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ ሊጠቀስ የሚችል አንድ ሙከራ ብቻ አስተናግዷል። በ36ኛው ደቂቃ ሠርካለም ባሳ በሳጥን ውስጥ የተቆጣጠረችውን ኳስ ወደ ግብ መትታ የአአ ከተማዋ ግብ ጠባቂ ስርጉት ያዳነችባት ብቸኛው የመጀመርያ አጋማሽ ሙከራ ነበር።
በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች እየተፈራረቁ አንፃራዊ የእንቅስቃሴ የበላይነት ሲወስዱ የታየ ሲሆን አርባምንጮች ከርቀት በሚሞከሩ ኳሶች ጎል ለማስቆጠር ሞክረዋል። በ52ኛው ደቂቃ ከርቀት የተሞከረው ኳስ የግቡን ብረት ገጭቶ የወጣው እና በ88ኛው ደቂቃ ፀጋነሽ ወረታ ከግብ ጠባቂዋ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝታ ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣባት ሙከራ በአርባምንጭ በኩል ሲጠቀስ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በጥቂት አጋጣሚዎች በደረሱት አዲስ አበዎች በኩል በ75ኛው ደቂቃ አስካለ ገብረፃድቅ ሳጥን ውስጥ ያገኘችውን ጥሩ አጋጣሚ ሞክራ ውጪ ወጥቶባታል።
ሀዋሳ ከተማ 0-1 ንግድ ባንክ
(በቴዎድሮስ ታከለ)
ተመጣጣኝ የሆነ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በተስተዋለበት ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ሀዋሳዎች በቅድስት ቴካ ላይ የተመሰረቱ ተሻጋሪ ኳሶች ላይ ቢያተኩሩም የሚፈጠሩትን እድሎች መጠቀም ሲሳናቸው ንግድ ባንኮች ከህይወት ደንጊሶ እና ትዕግስት ያደታ በቀጥታ ለአጥቂዎቹ ሽታዬ እና ረሂማ በመጣል ላይ አተኩረው ተጫውተዋል። በ7ኛው ደቂቃ ከሳጥኑ ጠርዝ ምርቃት ፈለቀ የግብ ጠባቂዋ ፍሬወይኒ ገብሩን መውጣት ተመልክታ ወደ ግብ የላከቻትን ኳስ የውስጥ ብረቱን ነክቶ ሲመለስ ጥሩ አንቺ መንገሻ በአስደናቂ ሁኔታ ያወጣችው ኳስ የጨዋታው የመጀመርያ እና ሀዋሳንም መሪ ሊያደርግ የተቃረበ ሙከራ ነበር፡፡ ባንኮች ከተደረገባቸው ሙከራ በኋላ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት የተጫወቱ ሲሆን በ15ኛው ደቂቃ ትዕግስት ያደታ በቀኝ በኩል ወደ ሳጥን ውስጥ ገብታ የሰጠችትን ብርቱካን ገብረክርስቶስ ብትመታውም ግብ ጠባቂዋ አባይነሽ ኤርቀሎ ስትተፋው ረሂማ ዘርጋው በድጋሚ መትታ አቅጣጫዋን ስታ ወደ ውጪ ወጥታለች፡፡
ምርቃት ከርቀት መትታ ፍሬወይኒ የያዘችባት፣ በ20ኛው ደቂቃ ቅድስት የፈጠረችላትን መልካም አጋጣሚ ምርቃት የባንክ ግብ ጠባቂ መውጣቷን ተመልክታ በመምታት ወደ ውጪ የወጣባት፣ እንዲሁም ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ ነፃነት ያገኘችውን ነፃ ያመከነችው በሀዋሳ በኩል የታዩ መልካም አጋጣሚዎች ነበሩ። በባንክ በኩል ደግሞ 35ኛው ደቂቃ ላይ ታሪኳ ዴቢሶ በግራ በኩል እየገፋች ገብታ የሰጠቻትን ኳስ በጥሩ አቋቋም ላየ የነቀረችው ረሒማ ዘርጋው መትታ አባይነሽ የያዘችባት ሙከራ ተጠቃሽ ነበር፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ንግድ ባንኮች በቅብብል ከሚገኙ አጋጣሚዎች በተለይ ከብርቱካን እግር ከሚነሱ ዕድሎች ወደ ሽታዬ እና ረሂማ ላይ በመጣል ግቦችን ለመፍጠር ጥረት ያደረጉበት ነበር። ሀዋሳዎች ደግሞ በተለይ ሳራ ኬዲ በ78ኛው ደቂቃ ላይ በጉዳት ተቀይራ ከወጣች በኃላ ተቀዛቅዘው ተስተውሏል። እንደ መጀመሪያው አጋማሽ አሁንም ቀዳሚ ሙከራ ማድረግ የቻሉት ሀዋሳዎች ነበሩ፤ ከማዕዘን የተሻማን ኳስ ትዝታ ኃይለሚካኤል በግንባሯ ገጭታ አግዳሚውን ነክቶ ወጥቶታል። 62ኛው ደቂቃ ላይ ምላሽ የሰጡት ባንኮች የማሸነፊያ ግባቸውን ማግኘት ችለዋል። ትዕግስት ወደ ግብ የላከችውን ኳስ የሀዋሳዋ ተከላካይ ምህረት ተስፋልዑል እና ግብ ጠባቂዋ አባይነሽ ኤርቀሎ ባለመናበባቸው ምክንያት ምህረት በግንባሯ ለማውጣት ስትሞክር በራሷ ላይ አስቆጥራ ንግድ ባንክን መሪ ማድረግ ችላለች፡፡
ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጫና ለማሳደር የሞከሩት ባንኮች ገነሜ ከራሷ ግብ ክልል እየነዳች ወደ ሀዋሳ ግብ ክልል ደርሳ ያቀበለቻትን ኳስ ብዙነሽ ሞክራ አባይነሽ የያዘችባት ተጠቃሽ አጋጣሚ ነበረች፡፡ አልፎ አልፎ ከሚገኙ ዕድሎች አቻ ለመሆን አማራጫቸው ያደረጉት ሀይቆቹ ምርቃት በተደጋጋሚ ወደ ግብ ክልል ብትደርስም በቀላሉ ሲባክኑባት ታይቷል፡፡ በጭማሪ ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ተሻምቶ ትዝታ በግንባር ገጭታ የግቡ አግዳሚ ለትሞ ሲመለስ ተከላካዮቹ ተረባርበው አውጥተውታል፡፡ ጨዋታውም በእንግዶቹ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።