ከፍተኛ ሊግ ሀ | ሰበታ መሪነቱን ሲረከብ ኤሌክትሪክ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ስምንተኛ ሳምንት ሁሉም ጨዋታዎች እሁድ ተደርገው ሰበታ ከተማ፣ ፌደራል ፖሊስ፣ ኤሪክትሪክ እና አክሱም ከተማ አሸንፈዋል። 

በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም በተከናወነ ጨዋታ አውስኮድ ከ ወሎ ኮምቦልቻ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል። ገና በጅማሮ የግብ ማግባት ሙከራዎች ያስተናገደው ይህ ጨዋታ የመጀመሪያውን ሙከራ በ5ኛው ደቂቃ አስተናግዷል። ሀቁ ምንይሁን ገዛህኝ ከቅጣት ምት ያሻማውን ኳስ ሳሙኤል አባተ በግምባሩ ሞክሮት የመጀመሪያ ጎል ለባለሜዳዎቹ ለማስቆጠር ቢሞክርም ግብ ጠባቂው ጀማል ዓሊ አምክኖበታል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ወሎ ኮምቦልቻዎች ለተሰነዘረባቸው ጥቃት ምላሽ ለመስጠት በኄኖክ ጥላሁን አማካኝነት ሙከራ ቢያደርጉም ኳስ እና መረብን ማገናኘት አልቻሉም። ከወትሮው በተለየ ጠንክረው የገቡት ባለሜዳዎቹ አውስኮዶች ሙክታር ሀሰን ከግራ መስመር አሻምቶት በነበረው ኳስ ግብ ለማስቆጠር ቢቀርቡም ኳሱ ግብ ጠባቂው ጀማልን አልፎ መረብ ላይ ሊያርፍ ሲል ተከላካዮች ተረባርበው ግብ ከመሆን ታድገውታል። አሁንም የግብ ማግባት ሙከራ ከማድረግ ያልቦዘኑት አውስኮዶች በ17ኛው ደቂቃ ወደ ግብ ሲደርሱ ጥፋት ተሰርቶባቸው የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። ፍቃዱ ታደሰ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ሀቁ ምንይሁን ገዛህኝ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን መሪ አድርጓል። ወደ አቻነት ለመመለስ በቶሎ ጥቃት የጀመሩት ኮምቦልቻዎች በ19ኛው ደቂቃ ጎል አስቆጥረው አቻ ሆነዋል። ከግራ መስመር መሬት ለመሬት የተሻማውን ኳስ የቀኝ መስመር ተከላካዩ ኄኖክ ከበደ በቀጥታ ወደ ጎል መቶ ቡድኑን አቻ አድርጓል።

አቻ ከሆኑ በኋላ ቀጥተኛ አጨዋወትን የመረጡት ባለሜዳዎቹ በ33ኛው ደቂቃ ረጅም ኳስ ለአጥቂዎቻቸው በመላክ ለግብ የቀረበ ሙከራ ሰንዝረው መክኖባቸዋል። ከ10 ደቂቃዎች በኋላም አውስኮዶች ከቆመ ኳስ ግብ አስቆጥረው ወደ መልበሻ ክፍል የሚያመሩበትን ጥሩ እድል አግኝተው ሳይጠቀሙ ቀርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ ባነሰ የግብ ሙከራ የቀጠለ ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች አቻን በመሻት ጥቃት መሰንዘራቸውን ቀንሰው ተጫውተዋል። ሁለቱም ቡድኖች እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ወደ ጎል ባይደርሱም ከቆሙ ኳሶች ግብ ለማስቆጠር ጥረዋል። በዚህም አውስኮዶች በ57ኛው ደቂቃ ግብ ባስቆጠረላቸው ሀቁ ምንይሁን አማካኝነት ከቆመ ኳስ ጥሩ ሙከራ አድርገዋል። 

ኮምቦልቻዎች ኳስን ተቆጣጥረው ለመጫወት በሞከሩበት የሁለተኛው አጋማሽ ክፍለ ጊዜ የአጥቂ እና የአጥቂ አማካኝ ተጨዋቾችን ቀይሮ በማስገባት ውጤቱን ወደ እንርሱ ለማምጣት ጥረዋል። በ79ኛው ደቂቃም ሄኖክ ከበደ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ነብዩ አህመድ በግምባሩ ሞክሮት ወደ ውጪ ወጥቶበታል። በ83 እና በ86ኛው ደቂቃዎች ሁለት ተከታታይ ሙከራዎችን በኤርሚያስ ኃይሌ እና በሠለሞን ጌድዮን አማካኝነት አድርገው የነበሩት አውስኮዶች ግብ ሳያስቆጥሩ ቀርተዋል። ሙሉ 90 ደቂቃው ተጠናቆ በጭማሪው ሰዓት ግልፅ የግብ ማግባት እድል ያገኙት ተጋባዦቹ ኮምቦልቻዎች በመልሶ ማጥቃት የአውስኮዶች የግብ ክልል ደርሰው ግብ ሳያስቆጥሩ ቀርተዋል።

አክሱም ላይ ወልዲያን ያስተናገደው አክሱም ከተማ 1-0 አሸንፏል። በሁለተኛው አጋማሽ በ65ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ቅጣት ምት ያገኙት አክሱሞች በወልዲያ ግብ ጠባቂ ግብ ከመሆን ሲከሽፍባቸው በ72 ኛው ደቂቃ የወልዲያ ግብ ጠባቂ ከፍያለው ኃይሉ ከግብ ክልል ውጭ ኳስ በእጁ በመንካቱ ከሜዳ በቀይ ካርድ ከሜዳ ሲወጣ የተሰጠውን ቅጣት ምትም ሐፍቶም ወደ ግብነት በመለወጥ አክሱም 1-0 አሸናፊ ሆኗል። 

ሰበታ ላይ ሰበታ ከተማ ቡራዩ ከተማን 3-0 በማሸነፍ ወደ መሪነት ከፍ ብሏል። ሁለት ተጫዋቾችን  እንዲሁም ዋና አሰልጣኙን በቅጣት ያጣው ሰበታ ከተማ በ33ኛው ደቂቃ ላይ ናትናኤል ጋንቹላ፣ በ43ኛው ደቂቃ ጫላ ዲሪባ እንዲሁም በ68ኛው ደቂቃ ላይ አዳነ ጎሎቹን ባስቆጠረው ጎል ማሸነፍ ችሏል። 

የምድቡ መሪ የነበረው ለገጣፎ ለገዳዲ በፌዴራል ፖሊስ 1-0 በሆነ ውጤት ተሸንፏል። ኦሜድላ ሜዳ ላይ በተደረገው ጨዋታ የመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መጠናቀቂያ ላይ በ45ኛው ደቂቃ ላይ ሰይፈ ዝክር ያስቆጠራት ጎል ለፌዴራል ፖሊስ 3 ነጥቦች አስገኝታለች።

ጎፋ ሜዳ ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ደሴ ከተማን አስተናግዶ 1-0 በማሸነፍ ካለፈው ሳምንት ሽንፈቱ አገግሟል። የኤሌክትሪክን ብቸኛ የድል ጎል በሁለተኛው አጋማሽ ያስቆጠረው አጥቂው ሐብታሙ መንገሻ ነው።

ሁለቱ አዳዲስ አዳጊዎች አቃቂ ቃሊቲ እና ገላን ከተማን ያገናኘው ጨዋታ ኒያላ ሜዳ ላይ ተካሂዶ ያለ ግብ ተጠናቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *