ከፍተኛ ሊግ ለ | ወልቂጤ፣ አአ ከተማ እና ኢኮስኮ ሲያሸንፉ መድን ነጥብ ጥሏል

በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ለ 8ኛ ሳምንት ከስድስቱ ጨዋታዎች አምስቱ ትላንት እና ዛሬ ሲከናወኑ ወልቂጤ ከተማ በግብጋሴው ቀጥሏል። ኢኮስኮ ከመመራት ተነስቶ ሲያሸንፍ መድን ነጥበ ጥሏል። 

በቴዎድሮስ ታከለ እና አምሀ ተስፋዬ

ቅዳሜ የተደረገው የዲላ ከተማ እና የነገሌ አርሲ ቡድን ጨዋታ በእንግዳው ቡድን ነገሌ አርሲ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። እጅግ ቀዝቃዛ እንቅስቃሴ የተሰተዋለበት የሁለቱ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ የሚደረጉት የነበረው እንቅስቃሴ ከመሐለኛው የሜዳ ክፍል መዝለል ያልቻለ ሲሆን በተለይም ባለሜዳው ቡድን ከግብ ክልል ኳስን መስርቶ ለሚሄድ የሚያድርገው ጥረት ቶሎ ቶሎ የሚቋረጥ ነበር። በ14ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ  ዝናው ዘላለም በራሱ ግብ ላይ ባስቆጠረው ግብ መምራት የቻሉት ነገሌ አርሲ በመከላከሉ ረገድ የተሻሉ በመሆን ውጤታቸውን ማስጠበቅ ችለዋል። በመጀመሪያው አጋማሽ ውጤቱን ለመቀልበስ ጥረት ያደረጉት ዲላ በቢንያም በቀለ እንዲሁም  ኢብራሂም ቢያኖ ያደረጉት የግብ ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።

በሁለተኛው አጋማሽ ውጤቱን ለመቀልበስ ጥረት ያደረጉት ባለ ሜዳዋቹ ዲላ ከተማዋች በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ቢደርሱም በራሳቸው የሜዳ ክፍል በቁጥር በዝተው የተጫወቱት ነጌሌዎች ክፍት ሳይሰጡ ቀርተዋል። በጨዋታው በቀኝ መስመር የነበረው ረዳት ዳኛ በ68ኛው ደቂቃ ላይ በስተግራ በኩል ኳሷ የእጅ ኳስ ወጥታ ባለችበት እና የዲላ ተጫዋቾች ባልነበሩበት ከጨዋታ ውጪ ማሳየቱ በርካታ ደጋፊዋችን ለተቃውሞ ያነሳሳበት ድርጊት የሚጠቀስ ክስተት ነበር።

ሀላባ ከተማ ሁለት የሜዳው ጨዋታዎችን በገለልተኛ ሜዳ እንዲያደርግ በተላለፈበት ቅጣት መሰረት ሀዋሳ ላይ በ7:00 አዲስ አበባ ከተማን አስተናግዶ 1-0 ተሸንፏል። ገና በጊዜ ምትኩ ማመጫ ከቅጣት ምት አክርሮ መትቶ ዋኬኔ አዱኛ በመለሰበት ሙከራ ጥቃት መፈፀም የጀመሩት ሀላባዎች ተጭነው በመጫወት በተደጋጋሚ የግብ ማግባት ዕድሎችን ለመፍጠር ችለዋል። በተለይ ካሳሁን ገረመው እና ምትኩ ማመጫ ወደ ፊት በአንድ ሁለት ቅብብሎሽ ቶሎ ቶሎ መድረስ ቢችሉም ወደ ውጤት ሊቀይር የሚችል የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች አለመኖሩ ለቡድኑ የጎላ ክፍተት እንደሆነ አይተናል፡፡ ብዙዓየው ሰይፈ ለሀላባ ውጤታማነት ሲያደርግ የነበረው ጥረትም አመርቂ ነበር። 20ኛው ደቂቃ ላይ ከአብዱላዚዝ የተሻረለትን ኳስ ካሳሁን ቢመታትም ኢላማዋን ስታ ወታበታለች፡፡ በ33ኛው አብዱላዚዝ ሞክሮ ብረት የመለሰበት ሙከራም ሀላባዎችን የምታስቆጭ ነበረች፡፡ 

አፈግፍገው መጫወትን ምርጫቸው ያደረጉት እና ለማጥቃት ሲያስቡ በሳዲቅ ሴቾ ላይ የተመሰረተ አጨዋወታት ባደረጉት አዲስ አበባዎች በመጀመርያው አጋማሽ የሚጠቀስ የግብ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። 35ኛው ደቂቃ ላይ የሀዋሳ ሰው ሰራሽ የመጫወቻ ሜዳ እጅጉን ፀሀይ በመበርታቱ ምክንያት ተጫዋቾቹ ለአንድ ደቂቃ የውሀ መጠጫ ጊዜ የተሰጠበት ክስተትም የመጀመርያው አጋማሽ ክስተት ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ የተወሰደባቸውን ብልጫ ማስመለስ ባይችሉም አዲስ አበባ ከተማዎች ተመጣጣኝ የሆነ እንቅስቃሴ አድርገዋል። በዚህም አጋማሽ ኳስ ተቆጣጥሮ በመጫወት ግብ ለማስቆጠር ተጭኖ ለመጫወት ሙከራ ያደረጉት ሀላባ ከተማዎች ናቸው፡፡ 69ኛው ደቂቃ  ካሳሁን ገረመው የሰጠውን መልካም አጋጣሚ ምትኩ ፊት ለፊት ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ሀላባን መሪ አደረገ ሲባል ዋኬኒ አዱኛ ሊይዝበት ችሏል፡፡ ያገኙትን ዕድሎች ወደ ግብነት መለወጥ ላይ ክፍተት የተስተዋለባቸው ሀላባዎች ግብ ሊቆጠርባቸው ችሏል፡፡ 74ኛው ደቂቃ  መልሶ ማጥቃትን የተጠቀሙት ምንያምር ጴጥሮስ ከቀኝ የሀላባ የግብ ክልል ያሻማትን ኳስ  ሳዲቅ ሴቾ ወደ ግብነት ለውጧት አዲስ አበባ ከተማን መሪ አድርጓል፡፡ 

ግብ ያስተናገዱት በርበሬዎቹ አጥቅተው በመጫወት ካሳሁን ገረመው በሚያደርጋቸው ጥረቶች አቻ ሊያደርጎቸው ይችሉባቸው የነበሩ ዕድሎችን አግኝተው ነበር፡፡ በ88ኛው ደቂቃ ላይ  በቀኝ በኩል የተሻገረን ኳስ ኤፍሬም ቶማስ በግንባር በመግጨት ግብ ቢያስቆጥርም ጥፋት ከግቡ በፊት ተፈፅሟል በሚል የእለቱ ዋና ዳኛ ግቧን ሽረዋታል፡፡ የግቧን መሻር ተከትሎ ሀላባዎች አግባብ አይደለም፤ እንዴት ረዳቱ ያፀደቀውን ዋና ዳኛው ይሽረዋል በማለት ክስ አስይዘው ጨዋታው ሊቀጥል ችሏል፡፡ 

በጭማሪ ደቂቃ ላይ የሀላባው ልመንህ ታደሰ እና የአዲስ አበባው ዓለማየሁ ሙለታ ተጋጭተው የወደቁ ሲሆን በልመንህ ታደሰ ላይ ከባድ የደም መፍሰስ በጭንቅላቱ ላይ በመድረሱ በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታል አቅንቷል፡፡ ዓለማየሁ ግን የመጀመሪያ ህክምና ከተደረገለት በኋላ ወደ ሜዳ ተመልሶ ተጫውቷል፡፡ የዳኛው ፊሽካ በሚጠበቅበት ሽርፍራፊ ሰከንድ መለሰ ትዕዛዙ ከግቡ ትይዩ ሆኖ ያገኛትን ተሻጋሪ ኳስ ወደ ግብ ለወጣት ሲባል ሳይጠቀምባት ቀርቶ ጨዋታው በአዲስ አበባ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ድሬዳዋ ላይ እንዲካሄዱ መርሀ ግብር ተይዞለት የነበረው የድሬዳዋ ፖሊስ እና የወልቂጤ እንዲሁም ናሽናል ሴሜንት ከ ኢትዮጵያ መድን ጨዋታዎች በከተማው በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ወደ ሀረር ተዘዋውሮ ቡድኖች ወደ ስፍራው ቢያቀኑም የሀረር ክልል አስተዳዳሪዎች ጨዋታው እንዳይካሄድ በመከልከላቸው በተስተካካይ ፕሮግራም ሊካሄድ ቢታሰብም የከፍተኛ ሊግ ኮሚቴ ባደረገው ጥረት ጨዋታዋቹ በድሬዳዋ ስታድዮም በዝግ ማካሄድ ተችሏል። በ4:00 ላይ ድሬዳዋ ፖሊስን ከወልቂጤ ያገናኘው ጨዋታ በወልቂጤ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል። በ25ኛው ደቂቃ አህመድ ሁሴን ለወልቂጤ ግብ አቆጥሮ መሪ መሆን ቢችሉም ድሬዳዋ ፖሊስ በፈርዓን ሰይድ አማካይነት አቻ መሆን ችሏል። ከዕረፍት መልስ አህመድ ሁሴን ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ መሪ መሆን የቻሉት ወልቂጤዎች በ67ኛው ደቂቃ ላይ ወጣቱ አብዱልከሪም ወርቁ ባስቆጠረው ጎል መሪነታቸውን አስፍተዋል። ድሬዳዋ ፖሊስ በፈርዓን ሰዒድ ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ቢችሉም ከሽንፈት መዳን አልቻሉም። ወልቄጤ በ7 ጨዋታ 18 ነጥብ በመሰብሰብ ምድቡን በአንደኝነት መምራቱን ቀጥሏል። 

እዚሁ ድሬዳዋ ላይ የተደረገው የናሽናል ሴሜንት እና ኢትዮጵያ መድን ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል። 

መድን ሜዳ ላይ ኢኮስኮ ከየካ ክፍለ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በኢኮስኮ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። የካዎች በንጉሴ ጌታሁን ግብ መሪ በመሆን የመጀመሪያውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ማጠናቀቅ ቢችሉም ከእረፍት መልስ ኢሳይያስ ታደሰ በ47ኛው እና በ53ኛው ደቂቃ አከታትሎ ባስቆጠራቸው ጎሎች ኢኮስኮ አሸንፎ መውጣት ችሏል። 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *