የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዝዮን 10ኛ ሳምንት ዛሬ በሦስት ጨዋታዎች ቀጥሎ ሲውል መከላከያ፣ አዳማ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።
8:00 አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክን የገጠመው ድሬዳዋ ከተማ 1-0 አሸንፏል። በጨዋታው ተመጣጣኝ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በተለይ በመጀመሪያ አጋማሽ ቢታይም ድሬዳዋ ከተማ በሁለተኛው አጋማሽ ብልጫን ወስደው በመጫወት አሸንፈው መውጣት ችለዋል፡፡
ሁለቱም ቡድኖች ኳስን ተቆጣጥረው ለመጫወት ከፍተኛ ጥረት ባደረጉት በመጀመሪያው አጋማሽ የሁለቱ ቡድኖች ምንም እንኳን ከሳጥን ውጪ በቀጥታ ወደ ግብ የሚላኩ ኳሶች ላይ የተገደበ ቢሆንም ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በተሻለ ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት አድርገዋል። በአንጻሩ ድሬዳዋ ከተማዎች በብቸኝነት ፊት መስመር ላይ የተሰለፈችው አይዳ ዑስማን ካደረገችው ሙከራ ውጪ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው እምብዛም ፍሬያማ አልነበረም፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ሁለቱም ቡድኖች በፍጥነት ወደ ጎል ለመድረስ ጥረት አድርገዋል። በተለይም ድሬዳዎች በዚህም በሁለተኛ አጋማሽ ተቀይራ ወደ ሜዳ የገባችው መቅደስ ማስረሻ ወደ ግብ የላከችትንና የኤሌክትሪኳ ግብ ጠባቂ ሠናይት አስረስ እንደምንም ግብ ከመሆን ያዳነችው ኳስ እንዲሁም አይዳ ዑስማን ከሳጥን ውጪ ተቆጣጥራ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ የላከቻትና ከግቡ አናት በላይ የወጣችባቸው ኳስ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ፡፡
ጫና ፈጥረው መጫወታቸውን የቀጠሉት ድሬዳዎች በ80ኛው ደቂቃ ላይ የጨዋታ የበላይነታቸው በስተመጨረሻም ፍሬ አፍርቶ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጫዋቾች ለማጥቃት በነቂስ በወጡበት ወቅት የተገኘውን የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ ተጠቃማ ትዝታ ፈጠነ በግሩም አጨራረስ ቡድኗን አሸናፊ ያደረገችውን ብቸኛ ግብ ማስቆጠር ችላለች፡፡
ከግቧ መቆጠር በኋላ የተነቃቁ የሚመስሉት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በ90ኛው ደቂቃ በቤተልሄም ከፍያለው አማካኝነት አቻ መሆን የሚችሉበት አጋጣሚያ ቢያገኙም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ድሬዳዎች በዛሬው የ1ለ0 ድል ታግዘው ነጥባቸውን ወደ 11 በማሳደግ ወደ 7ተኛ ደረጃ ከፍ ብለው ሲቀመጡ ኤሌክትሪኮች በ3 ነጥብ አሁንም በሊጉ ግርጌ ላይ ይገኛሉ፡፡
ረፋድ 4:00 ላይ መከላከያ ጥሩነሽ ዲባባን አስተናግዶ 4-1 አሸንፏል። ወጣቷ አማካይ አረጋሽ ከልሳ (ፎቶ ከላይ) ሦስት ጎሎትን አስቆጥራ ሐት-ትሪክ በመስራት ደምቃ ስታረፍድ መዲና ዐወል ቀሪዋን ጎል አስቆጥራለች። ለጥሩነሽ ዲባባ ደግሞ ቤተልሄም ሽመልስ ብቸኛዋን ኳስ ከመረብ አሳርፋለች።
አዳማ ላይ ጥረት ኮርፖሬትን ያስተናገደው አዳማ ከተማ 2-0 አሸንፏል። ሴናፍ ዋኩማ አንድ ጎል በማስቆጠር የግብ መጠኗን ዘጠኝ አድርሳ በከፍተኛ ጎል አስቆጣሪዎት ሰንጠረዥ ከአይዳ ዑስማን ጋር ቀዳሚ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ ሳራ ነብሶ የሌላኛው ጎል ባለቤት ናት።