በ13ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኢትዮጵያ ቡና በአዲስ አበባ ስታዲየም ጅማ አባ ጅፋርን ገጥሞ በአስቻለው ግርማ የጭንቅላት ግብ አንድ ለምንም ተሸንፏል። ከጨዋታው በኋላ በኢትዮጵያ ቡና በኩል ድህረ-ጨዋታ አስተያየት የሰጡት ምክትል አሰልጣኙ ገብረኪዳን ነጋሽ ሲሆኑ የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ በውጤቱ እጅግ ማዘናቸውንና ስለተከተሉት አጨዋወት ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ገልፀዋል።
” የዕለቱ ጨዋታ ፍጹም ከክለቡ የጨዋታ ባህል የተለየ ነበር። ይሁን እንጂ የትኛውም ልምምዳችን ላይ የዚህን አይነት ጨዋታ ልምምድ አለማድረጋችንን ላረጋግጥልህ እችላለው። እኔ የረዣዥም ኳስ አድናቂ አይደለሁም። የትኛውም ልምምድ ላይም ረዣዥም ኳስ አሰልጥኜ አላውቅም።”
አሰልጣኝ ጎሜስ ለሽንፈቱ ኃላፊነቱን እንደሚወስዱም ተናግረዋል። ” ያለፉትን ሶስት እና አራት ጨዋታዎቻችን በማየት ደጋፊው ሲበሳጭ እኔ እረዳለው። ነገር ግን የዛሬው ነጥብ ከማንም በላይ እኔን አበሳጭቶኛል። በምንም ነገር ማላከክ የምፈልግ ሰው አይደለሁም፤ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ እኔ ነኝ። ለውጤቱ 100% ኃላፊነቱን እኔ እወስዳለው። ይህ እግር ኳስ ነው፤ ነገም ሌላ ቀን ነው። በፍጥነት ስህተቶቻችንን አርመን ወደ ውድድር መግባት አለብን። ” ብለዋል።