ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ደደቢት ከ ስሑል ሽረ

የደደቢት እና የስሑል ሽረን ጨዋታ የተመለከቱ ነጥቦችን እንዲህ ተመልክተናቸዋል።

በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙት ስሑል ሽረ እና ደደቢት መጠነኛ ተስፋ ሊያስጨብጣቸው የሚችለውን ጨዋታ ዛሬ 09፡00 ላይ በትግራይ ስታድየም ያደርጋሉ። የመጨረሻ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ደደቢቶች በ12ኛው ሳምንት ወደ ቀድሞው ሜዳቸው አዲስ አበባ ስታድየም አቅንተው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ባደረጉት ጨዋታ 2-0 ተሸንፈዋል። ለመጨረሻ ጊዜ መቐለ ላይ ካደረጉት የአዳማው ጨዋታ አንድ ነጥብ ማግኘት ችለው የነበሩት ሰማያዊዎቹ ያሏቸው ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች ከሚገኙበት ደረጃ እንዲያወጧቸው ከዛሬው ጨዋታ የግድ ውጤት ማግኘት ይጠበቅባቸዋል። አሰልጣኝ ኤልያስ ኢብራሂም ከቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ በኋላ ቡድኑ ከጨዋታ ወደ ጨዋታ መሻሻል እያሳየ እንደሆነ የተናገረ ቢሆንም ወጣቶቹ ተጫዋቾች ከልምድ ማጣት የተነሳ በሜዳ ላይ የሚታይባቸው መደናገጥ እና መዘናጋት ቡድኑን ዋጋ እንዳያስከፍለውም ያሰጋል። በርግጥ የዛሬ ተጋጣሚያቸው ሽረ ያለበት ተመሳሳይ ሁኔታ ይህ ችግራቸው ጎልቶ እንዳይወጣ ሊያግዛቸው ይችላል። ደደቢት በልምምድ ላይ ጉዳት ከገጠመው ሙሉጌታ ብርሀነ ውጪ በዛሬው ጨዋታ የሙሉ ስብስቡን ግልጋሎት ያገኛል። 

በሜዳቸው ከሚያደርጓቸው ጨዋታዎች አንድ ነጥብ መልቀማቸውን የቀጠሉት አዲስ አዳጊዎቹ ስሑል ሽረዎችም ከደደቢት በአራት ነጥቦች ከፍ ብለው ይቀመጡ እንጂ ያሉበት ሁኔታ የተረጋጋ አይደለም። ክለቡ አሰልጣኞቹን እና የቡድን መሪውን ማገዱ የሚታወስ ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንት ደግሞ በብዛት ከሚጠቀምባቸው ሁለቱ አማካዮቹ ኄኖክ ካሳሁን እና ኪዳኔ አሰፋ ጋር ተለያይቷል። በርግጥ ከበላያቸው ያሉ ክለቦች በነጥብ እምብዛም አለመራቅ እና ያላቸው አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ለሽረዎች ተስፋ የሚሰጥ ቢሆንም ከሜዳ ውጪ ያለው ችግራቸውን በጊዜ ፈተው ትኩረታቸውን መሰብሰብ ይጠበቅባቸዋል። የዛሬው ጨዋታ በነጥብ ከሚበልጡት ክለብ ጋር የሚደረግ በመሆኑም የተሻለ በራስ መተማመር ኖሯቸው ወደ ሜዳ ሊገቡ እንደሚችሉ ይጠበቃል። የሸዊት ዮሃንስ ፣ ሰለሞን ገብረመድህን እና ንስሃ ታፈሰ ከጉዳት መመለስም ለቡድኑ ተጨማሪ መነቃቃትን ሊፈጥር እንደሚችል ይታመናል። ሆኖም የሳሙኤል ተስፋዬ መግባት አጠራጣሪ ሲሆን በጊዜያዊነት ወደ አሰልጣኞች ቡድን የተቀላቀለው መብራህቶም ፍስሃም ዛሬ ቡድኑን በሜዳ ላይ የማያገለግል ይሆናል። 

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ የፕሪምየር ሊግ የእርስ በርስ ግንኙነታቸውን ያደርጋሉ።

– በትግራይ ስታድየም አምስት ጨዋታዎችን ያደረገው ደደቢት ያሉት አራት ነጥቦች ያሳካው ከነዚሁ ጨዋታዎች ሲሆን በመጀመሪያዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ግን ሽንፈት ገጥሞት ነበር። 

– ስሐል ሽረ ከሜዳው ውጪ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ሲያሳካ 13 ግቦችን አስተናግዶ ሦስት አስቆጥሯል።

ዳኛ

– ከስድስተኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር ውስጥ ወላይታ ድቻ እና ደቡብ ፖሊስ የተገናኙበትን ጨዋታ ዳኝቶ ስምንት የማስጠንቀቂያ ካርዶችን የመዘዘው ዳንኤል ግርማይ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል። 

ግምታዊ አሰላለፍ

ደደቢት (4-2-3-1)

ረሺድ ማታውሲ

መድሀኔ ብርሀኔ – ዳዊት ወርቁ – ክዌኪ አንዶህ – ኄኖክ መርሹ

ኩማ ደምሴ – የአብስራ ተስፋዬ

ዳግማዊ ዓባይ – ዓለምአንተ ካሳ – አቤል እንዳለ

አሌክሳንደር ዐወት

ስሑል ሽረ (4-2-3-1)

ሰንደይ ሮቲሚ

አብዱሰላም አማን – ዘላለም በረከት  – ዲሜጥሮስ ወልደስላሴ – ክብሮም ብርሀነ

ሳሙኤል ተስፋዬ – ደሳለኝ ደባሽ

ሰዒድ ሁሴን – ጅላሎ ሻፊ – ልደቱ ለማ

ኢብራሂማ ፎፋና

                         

Leave a Reply