ባለፈው ዓመት በሁለተኛው ዙር ወልዋሎን በመያዝ ከቡድኑ ጋር የአንድ ዓመት ቆይታ ያደረጉት አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ዛሬ ከክለቡ ጋር በስምምነት ለመመያየት የይልቀቁኝ ጥያቄ አቅርበዋል።
በ2010 የውድድር ዓመት የካቲት ወር ላይ ወልዋሎ ዓ/ዩን በመረከብ በሊጉ እንዲቆይ ያስቻሉት አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ዘንድሮም ከክለቡ ጋር አብረው ቀጥለዋል። በዚህ ዓመት መጀመሪያ ቡድኑ መጥፎ አጀማመር ካደረገ በኃላም በተከታታይ ጨዋታዎች አሸንፎ ወደ ውጤት መንገድ በመመለስ ደረጃው ቢያሻሽልም ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ ዳግም ወደ ሽንፈት ተመልሷል። ያስተናገዳቸውን ሽንፈቶች ተከትሎም አሰልጣኙ ከአንዳንድ የክለቡ ደጋፊዎች ተቃውሞ ሲደርስባቸው መቆየቱ ይታወቃል።
በ11ኛው ሳምንት ባህርዳር ከተማን ከጨዋታ ብልጫ ጋር ካሸነፈ በኃላ ይታዩ የነበሩትን ተቃውሞዎችን ጋብ ማድረግ ችለው የነበሩት አሰልጣኙ ከሜዳ ውጪ ያሉት በርካታ ያልተፈቱ ጉዳዮች በቡድኑ ውጤት ፣ ተነሳሽነት እና አጠቃላይ የቡድን መንፈስ ላይ ከባድ ተፅዕኖ ማሳደራቸውን በመግለፅ ከክለቡ ጋር በስምምነት ለመለያየት ጥያቄ አቅርቧል። በዚህም መሰረት ክለቡ በቀጣይ ቀናት የሚሰጠው ምላሽ ይጠበቃል።
ወልዋሎ እስካሁን ካደረጋቸው አስራ ሁለት ጨዋታዎች አራት አሸንፎ ፤ አራት ጊዜ አቻ ወጥቶ በአምስት ጨዋታዎች ደግሞ ሽንፈት አስተናግዶ በዘጠነኛ ደረጃ ይገኛል።