የአሰልጣኞች አስተያየት | ወላይታ ድቻ 1-1 ባህር ዳር ከተማ 

ሶዶ ላይ የተከናወነው የወላይታ ድቻ እና ባህርዳር ከተማ ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

“በውጤቱ ደስተኛ ነኝ” ጳውሎስ ጌታቸው – ባህር ዳር ከተማ

ስለ ጨዋታው 

” በጠቃላይ ጨዋታው እጅግ በጣም ውጥረት የበዛበት እና እልህ አስጨራሽ የነበረ ነበር። ምክንያቱም እነሱም ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት እኛም ወደ መሪዎች ለመጠጋት የምንፈልገው ስለነበር ጠንካራ ነበር። ከእረፍት በፊት ተበልጠናል ፤ ከዕረፍት በኋላ ግን በልጠናል። እንዳያችሁትም ያለበለት ኳስ አምክነናል። መጨረሻ ላይ ደግሞ ሁለታችንም ተፈራርተናል። እኛም ውጤቱን ለማስጠበቅ አፈግፍገን ተጫውተናል። በአጠቃላይ በውጤቱ ደስተኛ ነኝ።”


በሁለተኛው አጋማሽ ስለቀየሩት አጨዋወት

“እንደሚታወቀው የኔ ቡድን ጥንካሬው በመስመር ማጥቃት ነው። ነገር ግን በመጀመርያ አጋማሽ ሁለቱም የመስመር አጥቂዎች ወደ ውስጥ እየገቡ ከጃኮ ጋር ይደረቡ ነበር። ያንን አርመን ነበር የገባነው። በሁለተኛ አጋማሽ በጣም ጥሩ ነበርን፤ እንዳያቹት ግርማ ዲሳሳ ያለቀ ኳስ ነው ያመከነው። በተደጋጋሚ ወደነሱ የግብ ክልልም ስንገባ ነበር። ወደ መጨረሻ ድካምም ስለነበረብን እና አየሩም ከብዶን ስለነበር ወደኋላ አፈግፍገን ውጤታችንን ይዘን ለመውጣት ጥረት አድርገናል። ”


ስለ ተጋጣሚ

” እኔ ወላይታ ድቻን ደጋፊውን ከዚህም በፊት ሃድያ ሆሳዕና እያለው በደንብ አውቀዋለው። እነ መሳይ ተፈሪ እና ዘነበ ጓደኞቼ ነበሩ። በተደጋጋሚ እዚህ እመጣለው፤ ለደጋፊውም ትልቅ ክብር አለኝ። ድቻ እንዳየሁት ውጥረት ውስጥ ነው ያለው። ከደጋፊዎችም ጫና እየደረሰበት እንደሆነ እየሰማው ነው። ነገር ግን እንደዚህ ጫና ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ የለባቸውም። ለዘነበም ጊዜ ሊሰጠው ይገባል። ተጫዋቹችም በስነልቦና ማጠንከር ነው ያለባቸው። ወላይታ ድቻ ሜዳው ላይም ከሜዳውም ውጪ የሚያሸንፍ ቡድን ነው። ቡድኑ የሚሰራ ቡድን ነው”


“እድል ከኛ ጋር አልነበረም” ዘነበ ፍስሀ – ወላይታ ድቻ


ስለ ጨዋታው

“ዛሬ ተጫዋቾቼ ለማሸነፍ ያላቸውን ሁሉ ሰጥተዋል። በባለፈው ጨዋታ ምክንያት ትልቅ ውጥረት ውስጥ ነው ያሉት። ውጤት ከመፈለግም አንፃር ያንንም ለመቀየር ማሸነፍ አለብን በሚለው ጭንቀት ውስጥ ነበሩ። እንደዛም ሆኖ ግን ጥሩ ተንቀሳቅሰዋል። እድል ከኛ ጋር አልነበረችም። በመጀመርያው አጋማሽ ላይ ጥሩ ነበርን፤ ግብም አስቆጥረናል። ግን አስጠብቀን ለመውጣት ከመፈለግ አንፃር ወደ ኋላ ማፈግፈግ አለ። ይሄ በፍፁም ተገቢ አይደለም። በዛም ምክኒያት ነው ግብ እየተቆጠረብን ያለው። ከተጫዋቾቼ ጋርም ይሄን ለማረም እንሰራለን።”


ቡድን ላይ ሰለሚስተዋለው የሥነ-ልቡና ችግር

“የቡድኑን ሥነ-ልቡና ለመገንባት ከትላንት በስቲያ ባለሞያ በማምጣት በጥሩ ሁኔታ ሲረዱን ነበር። በቋሚነትም ባለሞያ ለመቅጠር ቡድኑ ይንቀሳቀሳል። በቀጣይ ከሜዳችኝ ውጪ አዳማን ስንገጥም ያለንን ሁሉ ሰጥተን እንጫወታለን።”


ከደጋፊው ሰለሚመጣው ጫና

“አዎ ደጋፊው የሚያነሳው ነገር በጣም ትክክል ነው። ውጤትን ከመፈለግ አንፃር ነው። ደጋፊ ሜዳ የሚገባው ውጤት ፈልጎ ነው። እኛም ውጤት የማምጣት ግዴታ አለብን፤ ደጋፊ ውጤት ፈልጎ ነው እንጂ ቡድኑን ለመረበሽ አይደለም። ነገር ግን አንዳንዴ ግለሰብች ላይ ሲሆን ትንሽ ተጽዕኖ አለው። ደጋፊው ትክክል ነው፤ ይሄን ተቀብለናል ከተጫዋቾቼም ጋር በደምብ አስረግጠን ተማምነናል። ውጤት ማምጣት የግድ ነው። “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *