በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ለ8ኛ ሳምንት ምድብ ለ ቀሪ አንድ ጨዋታ ዛሬ ዱራሜ ላይ ተካሂዶ ሀምበሪቾ ወላይታ ሶዶን 4-1 በማሸነፍ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችሏል።
ከፋ ዞን ላይ ህይወታቸው ያጡ የከምባታ ተወላጆን ለማሰብ የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማድረግ የተጀመረው ጨዋታ በፌዴራል ዳኛ ዓለማየሁ ለገሰ በጥሩ ብቃት የተመራው ሲሆን ተቀዛቅዞ ተጀምሮ ቀስ በቀስ ጥሩ ፉክክር ታይቶበታል። ወደፊት ለመጓዝ እምብዛም ያልደፈሩት ሶዶዎች ግብ በማስቆጠር ረገድ ቀዳሚ ነበሩ። ሰለሞን ጌታቸው በ13ኛው ደቂቃ የሀምበሪቾን ተከላካይ ክፍል ስህተት ተጠቅሞ የቀማውን ኳስ ወደ ግብ ክልል ይዞ ሲገባ በተሰራበት ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ብሩክ አማኑኤል መትቶ ግብ ጠባቂው አስራት ሚሻሞ ቢያድነውም በቅርብ ርቀት የነበረው መሳይ አገኘው ወደ ግብነት ለውጦታል።
ከግቡ መቆጠር በኋላ የአቻነት ግብ ፍለጋ ተጭነው ለመጫወት ሙከራ ያደረጉት ሀምሪቾዎች ኳስን ከግብ በመመስረት ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ መድረስ የቻሉ ሲሆን በ20ኛው ደቂቃ ዘካርያስ ፍቅሬ ወደ ግብ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሲያድንበት በ22 ኛው ደቂቃ ዘካርያስ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን ቅጣት ምት ወንድሜነህ ዘሪሁን ወደ ግብነት በመለወጥ ሀምበሪቾን አቻ ማድረግ ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ይበልጥ መነቃቃት የታየባቸው ሀምበሪቾዎች በተደጋጋሚ የሶዶን ግብ ክልል ሲፈትሹ ታይተዋል። በተለይም በ29ኛው ደቂቃ በረከት አዲስ ከመቆያ አልታየ የተሻገረትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ በግቡ አናት የወጣችበት አጋጣሚ እንዲሁም በ33ኛው ደቂቃ ፋሲል ባቱ በግል ጥረቱ ሁለት ተጫዋቹችን አልፎ የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ ከፍ አድርጎ የመታው ኳስ ግብ ጠባቂው ያዳነበት ይጠቀሳሉ። በ43ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በረከት ቦጋለ ያሻማውን ኳስ በነፃ አቋቋም ላይ የነበረው አብነት ተሾመ በግንባሩ በመግጨት ሀምበሪቾን ወደ መሪነት አሸጋግሮ የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል።
በሁለተኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተሻሽለው የገቡት ወላይታ ሶዶዎች በተለይ በመጀመርያዎቹ አስር ደቂቃዎች በሀምበሪቾ የሜዳ ክፍል አመዝነው ኳስ መቆጣጠር እና የግብ ሙከራ ማድረግ ችሀዋል። በ48ኛው ደቂቃ ዳግም ማቴዎስ እና በ54ኛው ደቂቃ አሸናፊ ዋሎ ያደረጉት የግብ ሙከራም ተጠቃሽ ነበር።
ባለሜዳው ሀምበሪቾ ወደ ኋላ ቢያፈገፍግም በመልሶ ማጥቃት የሚፈጥረው ጫና በ60ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬ በማፍራት የሶዶዎችን የተከላካይ ስህተት ተከትሎ ፋሲል ባቱ ያሻገረውን ኳስ ዘካርያስ ወደ ግብነት ለውጦ የግብ ልዩነቱን ወደ ሶስት ከፍ ማድረግ ችሏል። በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ የገባው አላዛር አድማሱ የሶዶን የግራ መስመር በመስበር የሚፈጥረው ጫና ከፍ ያለ የነበረ ሲሆን በ85ኛው ደቂቃም በሱ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ዘካርያስ ፍቅሬ ወደ ግብነት ለውጦ ጨዋታውም 4-1 ተጠናቋል።