ደቡብ ፖሊስ ጊዜያዊ አሰልጣኝ ሾመ

ከዘላለም ሽፈራው ጋር ከአምስት ወራት ቆይታ በኋላ በስምምነት የተለያየው ደቡብ ፖሊስ የቀድሞው የክለቡን ተጫዋች አላዛር መለሰን በጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝነት ሾመ፡፡
ወደ ፕሪምየር ሊጉ ከ8 ዓመታት በኋላ ዳግም የተመለሰው ደቡብ ፖሊስ በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው እየተመራ የሊጉን ጉዞ ቢጀምርም ውጤታማ ያልሆነ የውድድር ጊዜን እያሳለፈ በመገኘቱ ከአሰልጣኙ ጋር ቀሪ የ7 ወራት ውል እያለው መለያየታቸው የሚታወስ ሲሆን በረዳት አሰልጣኞቹ ያለው ተመስገን እና አዲሱ ጡኔ ይመራሉ ተብሎ የነበረ ቢሆንም ክለቡን በተሻለ ብቃት ሊመራ ይችላል በሚል የቀድሞው ተጫዋች አላዛር መለሰን በጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝነት ሾሟል፡፡

በ1990ዎቹ ጅማሮ በአሰልጣኝ ከማል አህመድ በሚመራው ሀዋሳ ከተማ የእግር ኳስ ህይወቱን የጀመረው አላዛር በመቀጠል በሻሸመኔ ከተማ፣ ይርጋለም እና ከስምንት ዓመት በፊት በነበረው የደቡብ ፖሊስ ስብስብ ውስጥ በተጫዋችነት አሳልፏል፡፡ በተከላካይ እና አማካይ ቦታዎች ላይ የተጫወተው አላዛር በ1992 ለታዳጊ ብሔራዊ ቡድንም ተመርጦ ጨዋታ አድርጓል። በአሰልጣኝነት ደግሞ ደቡብ ፖሊስ በከፍተኛ ሉጉ በአሰልጣኝ ቾንቤ ገብረህይወት በሚመራው የ2007 ቡድን ውስጥ በረዳት አሰልጣኝነት የሰራ ሲሆን ያለፉትን ሁለት ዓመታት ደግሞ የደቡብ ፖሊስ የታዳጊ ቡድን እና የከማል አካዳሚ ውስጥ ሲሰራ ቆይቷል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *