ዕልባት ማኔጅመንት ቴክኖሎጂ ሶሉሽን ‘ቲፎዞ’ የተሰኘ የተቀናጀ ዲጂታል የስፖርት ፕላትፎርም ከፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብ እና የደጋፊዎች ማኅበር ጋር በመተባበር ተግባራዊ ማድረግን በሚመለከት ዛሬ ከሰዓት ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጥ ሁለቱ ወገኖችም የ5 ዓመት ውል ተፈራርመዋል።
ዛሬ 11:30 ላይ በጎንደር ቋራ ሆቴል የክለቡ ስራ አስኪያጅ፣ የቦርድ ኃላፊዎች፣ የደጋፊ ማኅበር አመራሮች፣ ጋዜጠኞች እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት የተደረገውን ይፋዊ የፊርማ ስነስርዓት አቶ መክት ካሳሁን፤ የደጋፊዎች ማኅበር የሒሳብ ሹም በንግግር ከከፈቱ በኋላ የዲጂታል ስፖርት ፕላትፎርም ለፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብ እና ደጋፊዎች ማኅበር የሚያስገኛቸው ጥቅሞች ተዘርዝረዋል።
– በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ በሀገር ውስጥም ሆነ በዉጭ ያሉ ደጋፊዎችን መመዝገብ እና መዋጮ ለመሰብሰብ ያስችላል ።
– የተመዘገቡና መታወቂያ የያዙ ደጋፊዎችን ቁጥር ይጨምራል ።
– የደጋፊዎች ማኅበር የደጋፊዎችን ቁጥር ያገናዘበ የተለያዩ የማርኬቲንግ ስራዎች ለመስራት እድል ይፈጥራል።
– የደጋፊዎች ማኅበር ስፖርት ክለቡን በፋይናንስ ለመደገፍ በሚደረገው እንቅስቃሴ ዉስጥ ጉልህ ድርሻ ይይዛል ።
– ዘመናዊ የሆነ እና ጊዜው የሚጠይቀው ብራንድ እንዲኖረዉ ያደርጋል።
– የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ስራዎችን በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ ለማከናወን ያስችላል።
– የክለቡን ገቢ ይጨመራል የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
በመቀጠል ንግግር ያደረጉት የዕልባት ማኔጅመንት ዋና ዳይሬክተር አቶ ነፃነት ራያ ስለ ቴክኖሎጂው እና ተያያዥ ጉዳዮች ማብራሪያ ሰጥተዋል። ” በመጀመሪያ ደረጃ ከዐፄዎች ጋር ይሄን ውል ፈፅመን ስራ እንድንሰራ ስለተደረገልን ትብብር እና መልካም ፍቃድ ያለንን አክብሮት አንዲሁም አድንቆት መግለፅ እፈልጋለሁ። ይህ “ቲፎዞ” የተባለው የተቀናጀ የዲጂታል ስፖርት ፕላት-ፎርም ቴክኖሎጂ ነው። ይሄንን ሀሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥናት በማድረግ እና ተፈፃሚ በማድረግ እልባት ማኔጅመንት እና ቴክኖሎጂ ሶልዩሽን ምናልባትም ከፈፀማቸው እና ከሚኮራባቸዉ አንዱ ፕሮጀክት ነው። ይሄ ፕሮጀክት ስፖርት ቢዝነስ የሚለው ጽንሰ ሐሳብ መጎልበት ላይ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ይሄን ስራ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ተፈፃሚ ያደረግነው ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ሲሆን ሁላችሁም እንደምታዉቁት በቀጣይ ደግሞ ከአዲስአበባ ውጭ በክልሎች ላይ ፋሲል ከነማ የመጀመሪያው ክለብ ይሆናል። ብዙ ስራዎችም እንዲሁ የምንሰራ ይሆናል። ”
” በቲፎዞ ቴክኖሎጂ እንግዲህ በዋነኛነት 4 ዋና ዋና ስራዎችን ነው ምንሰራው። አንደኛዉ የአባላት ምዝገባን ዘመናዊ ማድረግ ነው። አሁን ያለዉ የአባላት ምዝገባ በፅህፈት ቤት እየመጡ የሚደረግ ነው፤ ነገርግን በሞባይል ቴክኖሎጂ በመታገዝ በያሉበት የግድ ፅህፈት ቤት በአካል ሳይመጡ ዲጅታል የአባልነት ምዝገባ ራሳቸውን መመዝገብ እንዲሁም ደግሞ በየአካባቢው ባሉ ኤጀንቶች አዲስ አበባን ጨምሮ በውጭ ሀገራት ደጋፊዎች በሚበዙበት አካባቢ ያሉ ቀጥታ የአባላት ዲጅታል ምዝገባ ማድረግ የሚችሉበት ነው። ሁለተኛው የወርሃዊ መዋጮ ከየትኛውም አካባቢ በቀጥታ መክፈል የሚችሉበት ስርዓት ነው። ሶስተኛው የዲጅታል ካርድ አቅርቦት ሲሆን አንድ ደጋፊ የስታድየም እና የጉዞ ትኬት ክፍያ ማስፈፀም የሚያስችል ካርድ ይሰጠዋል። አራተኛው ማልያ እና ሌሎች ክለቡ ለገቢ ማስገኛ ብሎ የሚሸጣቸውን ቁሳቁሶች በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ በኦንላይን መሸጥ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው። በአጠቃላይ ይሄ ስራ ዛሬ ከተፈረመበት ቀን ጀምሮ ምናልባትም በሶስት ወይም አራት ሳምንት ጊዜ ዉስጥ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ይደረጋል። ተግባራዊ የሚደረገዉ በጎንደር ብቻ ሳይሆን በጥናት በተደገፈ መልኩ የፋሲል ደጋፊዎች በሚበዙበት አካባቢ ላይ ይሄንን ቴክኖሎጅ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተመዘገቡ ደጋፊዎች ቁጥር እንዲበዛ፤ ይሄ ብቻም ሳይሆን ገቢም በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል ብለን እናስባለን። በአጭሩ ቲፎዞ ቴክኖሎጅ ይሄን ይመስላል። ” ሲሉ ሰፊ ማብራርያ ሰጥተዋል።
የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ፍስሀ አገኘሁ በበኩላቸው ” የፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብን ለማዘመን በማስብ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ዉጤቶችን ተግባራዊ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰን ነዉ ያለነው። ፋሲል ወደ ህዝባዊነት ተቀይሮ ወይንም ደግሞ ህዝባዊነትን ተላብሶ የራሱ ገቢዎችን በማመንጨት እና ዘላቂነት ያለው ክለብ እንዲሆን ነው ጥረት እያደረግን የምንገኘው። ለለውጥ በምናደርገው እንቅስቃሴ ላይ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት በመፍጠር የቢዝነስ ከባቢ በመፍጠር ክለቡ ራሱን ችሎ በሁለት እግሩ የሚቆምበትን ሁኔታ እያመቻቸን ነው ያለነው። የዚህ እንቅስቃሴ አንደኛው አካል ከዕልባት ቴክኖሎጅ ጋር የምናደርገው የውል ስምምነት ነው። ይሄ ሂደት እንዲሳካ የክለቡ የደጋፊ ማኅበር አና በዓለም ዙርያ የሚገኙ ደጋፊዎች አይዞህ ባይነት አስፈላጊ ነው። የቴሌኮም ቴክኖሎጂ ኩባንያው ተነሳሽነት ኖሮት ራሱ ነዉ የመጣው። ስለዚህ ይህንን ጅምሩን ለስኬት ለማብቃት አሁንም ከነእርሱ ጥረት፣ ታማኝነት እና ኃላፊነት ይጠበቃል። ስለዚህ ከእኛ ጋር በእምነት እና በጥንካሬ አብሮ ከተጎዘ ሁለታችንም ስኬታማ እና አሸናፊ እንሆናለን ብለን እናስባለን። ይሄን በማስመልከት ክለባችን ውል እንደሚፈራረም ማሳወቅ እፈልጋለሁ። ” ብለዋል።
በመጨረሻም የደጋፊዎች ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ጋሻዉ አስማረ ባደረጉት ንግግር ” ከዕልባት ጋር ያደረግነው ስምምነት ከብዙ የተንዛዙ አሰራሮች ወጥተን ወደ ቴክኖሎጂ እንድንገባ ያደርገናል። ከተጠያቂነት አንፃር ቅን በሆነ ወይም ደግሞ ለብዙዎች ግልጽ በሆነ መንገድ ለመስራት የሚረዳን ሁኔታ ስለሆነ ለኛም የተሻለ ነው። በውጭ የሚኖሩ ደጋፊዎች ብዙዎቹ አባል መሆን እፈልጋለን እያሉ ይደውሉልናል። እነሱንም ተጠቃሚ ማድረግ ስለሚያስችል እነርሱም ድጋፍ የሚያደርጉበትን መንገድ እና የተሻለ ፋይናንስ የምንሄድበትን መንገድ እዚህ ድርጅት ጋር ለመስማማት በመብቃታችን እንደ ደጋፊ ምስጋና ማቅረብ እንፈልጋለን። እነዚህ ነገሮች እንዲሳኩ እኛም የምናደርጋቸው የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴዎች ይኖራሉ፤ ድርጅቱም እንደዛው። አሁን ካለንበት የአባለት ቁጥር በብዙ ሺህ እጥፍ እንደሚጨምር ነው የምናስበው። ” ብለዋል።
የፕሮግራሙ ፍፃሜ ላይ የቋራ ሆቴል ባለቤት በዝግጅቱ ላይ ለታደሙ እንግዶች የእራት ግብዣ አድርገው የዕለቱ መርሐ ግብር ተፈፅሟል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡