ከነገ ጨዋታዎች መካከል ቻምፒዮኖቹ ባህር ዳርን የሚያስተናግዱበት ጨዋታ የዛሬ ቅድመ ዳሰሳችን የመጀመሪያ ትኩረት ነው።
በአፍሪካ መድረክ ተሳትፏቸው ምክንያት ዝቅተኛ ቁጥር ያላቸው ጨዋታዎች (8) ያደረጉት ቻምፒዮኖቹ ጅማ አባ ጅፋሮች በሦስተኛው የሜዳ ጨዋታቸው ነገ 09፡00 ላይ ከባህር ዳር ከተማ ይገናኛሉ። ፊታቸውን ወደ ሊጉ በመለሱበት ወቅት ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን ማሸነፍ የቻሉት አባ ጅፋሮች በጨዋታዎቹ ግብም አልተቆጠረባቸውም። ከተስተካካይ ጨዋታዎቻቸው ጭምር የአምናውን ግስጋሴያቸውን መድገም የሚያስችል ጉዞ ላይ የሚገኙት ጅማዎች የነገው ጨዋታ የደረጃ መሻሻል የሚያመጣላቸው ባይሆንም ከበላያቸው ወዳሉት ክለቦች ሊያቀርባቸው ይችላል። ሊጉን በጀመሩበት ፍጥነት እየቀጠሉ የማይገኙት ባህር ዳር ከተማዎች ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ሁለት ነጥቦችን ብቻ ማግኘታቸው ከሰንጠረዡ አጋማሽ ከፍ እንዳይሉ አድርጓቸዋል። በርግጥ ሁለቱ ጨዋታዎች ከሜዳ ውጪ የተደረጉ መሆናቸው ሲታይ ውጤቱን የከፋ የማያደርገው ሲሆን የጣና ሞገዶቹ ከጅማ በድል ከተመለሱ የነጥብ ድምራቸውን ወደ 20 በማድረስ የተወሰኑ ደረጃዎችን ከፍ የማለት ዕድል ይኖራቸዋል።
ጉዳት ላይ የሚገኘው የጅማ አባ ጅፋሩ ግብ ጠባቂ ዘሪሁን ታደለ እና ህመም ላይ የቆየው ከድር ኸይረዲን እንዲሁም በቡናው ጨዋታ ጉዳት ገጥሞት ተቀይሮ የወጣው ዐወት ገብረሚካኤል ለነገው ጨዋታ አይደርሱም። ከዚህ ውጪ በግል ጉዳይ ወደ ሆላንድ ያቀናው ዳንኤል አጄዬ ከነገው ስብስብ ውጪ ሲሆን ከጉዳት እና ከህመም የተመለሱት ኤልያስ አታሮ እና ያሬድ ዘውድነህ እንዲሁም መጠነኛ ጉዳት ያለበት አስቻለው ግርማ ለጨዋታው መድረሳቸው አጠራጣሪ ሆኗል። በባህርዳር ከተማ በኩል ደግሞ ዳንኤል ኃይሉ እና ማራኪ ወርቁ ከጉዳት ያልተመለሱ ሲሆን እንዳለ ደባልቄ ደግሞ ከጉዳት ቢያገግምም ልምምድ ባለሟሟላቱ የነገው ጨዋታ ያልፈዋል።
ጅማ አባ ጅፋር ጨዋታውን ሜዳው ላይ እንደማከናወኑ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ለማግኘት በመሞከር በመስመር አጥቂዎቹ በኩል ወደ ባህር ዳር የግብ ክልል ለመግባት እንደሚያቅድ ይጠበቃል። በመሆኑም በፈጣን ሽግግር ወደ ፊት ለመድረስ ይሞክርበት ከነበረው የቡናው ጨዋታ የተለየ መልክ ሊኖረው ይችላል። በአንፃሩ ይህንኛውን መንገድ ባህር ዳሮች ሊጠቀሙበት የሚችሉበት ዕድል የሰፋ ነው። የጣናዎቹ ሞገዶች በሁለቱ ክንፎች ካሏቸው አጥቂዎች አንፃር ሲታይም ጉዳት ባጠቃው የባለሜዳዎቹ የሁለቱ መስመሮች የተከላካይ ክፍል ፈተና ሊሆኑ ይችላሉ። ከዚህ ውጪ የዳንኤል አጄዬ አለመኖርም በጅማ በኩል የሚፈጥረው ክፍተት በቀላሉ የማይታይ ሲሆን በኋላ ክፍሉ ክፍተቶች ኖረውበትም ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ግብ ሳይቆጠርበት መውጣቱ ግን በመልካም ጎን የሚነሳ ነጥብ ነው።
የእርስ በርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች
– ሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ ታሪክ የመጀመሪያ የእርስ በርስ ግንኙነታቸውን ያደርጋሉ።
– እስካሁን ጥቂት ጨዋታዎችን (ሁለት) ሜዳው ላይ ያደረገው ጅማ አባ ጅፋር አንድ የድል እና አንድ የአቻ ውጤቶችን አስመዝግቧል።
– ባህር ዳር ከተማ ስድስት ጨዋታዎችን ከሜዳው ውጪ አድርጎ ሁለት ጊዜ ሽንፈት ሲገጥመው ከቀሪዎቹ ጨዋታዎች ስምንት ነጥቦችን አሳክቷል። ቡድኑ በነዚህ ጨዋታዎች ግብ ሳያስቆጥር የወጣው በአንድ አጋጣሚ ብቻ ነበር።
ዳኛ
– በአምስት ጨዋታዎች አራተኛ ዳኛ ሆኖ የተመደበው ተከተል ተሾመ አራት የቢጫ ካርዶች ከመዘዘበት የአምስተኛው ሳምንት የስሑል ሽረ እና ጅማ አባ ጅፋር ጨዋታ በኋላ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)
ሚኪያስ ጌቱ
ኄኖክ ገምቴሳ – መላኩ ወልዴ – አዳማ ሲሶኮ – ተስፋዬ መላኩ
ይሁን እንዳሻው – አክሊሉ ዋለልኝ – መስዑድ መሀመድ
ዲዲዬ ለብሪ – ማማዱ ሲዲቤ – አስቻለው ግርማ
ባህርዳር ከተማ (4-3-3)
ሐሪስተን ሄሱ
ሣለአምላክ ተገኝ – ወንድሜነህ ደረጄ – አቤል ውዱ – አስናቀ ሞገስ
ዳንኤል ኃይሉ – ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – ኤልያስ አህመድ
ወሰኑ ዓሊ – ጃኮ አራፋት – ግርማ ዲሳሳ
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡