ወልዋሎ ናይጀርያዊ አጥቂ አስፈረመ

ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲዎች የዝውውር መስኮቱ ከመዘጋቱ በፊት ለማስፈረም የተስማሙትን ናይጀርያዊ አጥቂ የግላቸው ማድረጋቸውን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጧል፡፡

በዚህ ዓመት ሁነኛ የአጥቂ ክፍል ተሰላፊ ያላገኙት ቢጫ ለባሾቹ አመዛኙ የእግር ኳስ ህይወቱን በህንድ ያሳለፈው ናይጀርያዊ የሃያ ሰባት ዓመት አጥቂ ክሪስቶፈር ቺዞባን አስፈርመዋል። የእግርኳስ ህይወቱን በሰሜን ህንዱ ክለብ ካልያት ሚላን ሳንጋ የጀመረው ይህ ናይጀርያዊ አጥቂ በሎኔስታር ካሽሚር እና በታሪካዊው የህንድ ክለብ ሞሃን ባጋን ተጫውቶ ያሳለፈ ሲሆን ከዛ በተጨማሪ በማይናማር ቆይታው ለአይዋድይ ዩናይትድ እና ሻን ዩናይትድ ተጫውቷል።

በ2016 ማርቱ ናህ ከተባለው ተጫዋች በጣምራ እንዲሁም በ2017 በተመሳሳይ ከሌሎች ሁለት ተጫዋቾች ጋር በጋራ የማይናማር ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ ያጠናቀቀው ይህ ግዙፍ ተጫዋች በፊት መስመር ተሰላፊ እጦት ለተቸገረው የፀጋዬ ኪዳነማርያም ስብስብ መፍትሄ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

ወልዋሎ ከዳዊት ፍቃዱ ጋር መለያየቱን ተከትሎ ቀሪውን የአንደኛ ዙር በጉዳት እየተቸገረ በሚገኘው ሪችሞንድ አዶንጎ ላይ ጥገኛ ሆኖ የሚቆይ ሲሆን በሁለተኛው ዙር የናይጄሪያዊውን ግልጋሎት ማግኘት ይጀምራል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *