ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

አዳማ እና ድቻ በሚያደርጉትን የነገ የ14ኛ ሳምንት ጨዋታ ዙሪያ የሚነሱ ጉዳዮችን በቅድመ ዳሰሳችን እንስመለክታችኋለን።

በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም 09፡00 ላይ በሚጀምረው የነገ ጨዋታ ከ13ኛው ሳምንት አንድ ነጥብ ማግኘት የቻሉት አዳማ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ይገናኛሉ።
ከፋሲል ከነማ ጋር ያለግብ የተለያየው አዳማ ከተማ ከሰባተኛው ሳምንት በኋላ ሽንፈት ሳያስተናግድ ከስድስት ጨዋታዎች 16 ነጥቦች አሳክቷል። እንደ ደካማ አጀማመሩ ባይሆን ኖሮም አሁን ካለበት የሰባተኛ ደረጃ ከፍ ባለ ነበር። ሆኖም ነገ ማሸነፍ ከቻለ ከበላዩ ባሉት ክለቦች ውጤት ላይም ተመስርቶ እስከሶስተኝነት ከፍ የማለት ዕድል ይኖረዋል። ከተጋጣሚያቸው በተቃራኒ ከስድስተኛው ሳምንት በኋላ የድል መንገዱ የጠፋባቸው ወላይታ ድቻዎች አሁንም በደካማ ጉዟቸው ሲቀጥሉ ሳምንት ባህር ዳር ከተማን ባስተናገዱበት ጨዋታ መምራት ቢችሉም በቀድሞው አጥቂያቸው ጃኮ አራፋት ግብ ነጥብ ለመጋራት ተገደዋል። ነገም በታሪካቸው ምንም ነጥብ አሳክተውበት ወደማያውቁበት ስታድየም የሚያዱርጉት ጉዞ ቀላል እንደማይሆን ሲገመት በለስ ከቀናቸው ግን ከወራጅ ቀጠናው ያላቸውን የነጥብ ርቀት ውደ አራት ከፍ የማድረግ ዕድል ይኖራቸዋል።

አዳማ ከተማ አማካዩ ኤፍሬም ዘካሪያስ ከረጅም ጊዜ በኃላ ከጉዳቱ አገግሞ ወደ ሜዳ ሲመለስለት አንዳርጋቸው ይላቅ እና ሱራፌል ጌታቸውም ከጉዳት ተመልሰው ወደ ልምምድ ቢገቡም በቂ ዝግጅት ጊዜ ያልነበራቸው በመሆኑ ለነገው ጨዋታ አይደርሱም። በተጨማሪም ቡልቻ ሹራ በወልዋሎው ጨዋታ በተመለከተው ቀይ ካርድ የማይሰለፍ ሲሆን የብርድ ህመም ያስተናገደው ወሳኙ አጥቂ ዳዋ ሆቴሳ የመሰለፍ ጉዳይም አለየለትም። በወላይታ ድቻዎች በኩል ደግሞ በብዛት በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ከሚያካትቷቸው ተጫዋቾች መካከል ፣ ፍፁም ተፈሪ ፣ አንዱዓለም ንጉሴ ፣ እዮብ አለማየሁ እና ግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነት በጉዳት ወደ አዳማ አላመሩም፡፡

የእርስ በርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– ሁለቱ ክለቦች እስካሁን በሊጉ ስምንት ጊዜ ያህል የተገናኙ ሲሆን በአቻ ውጤት የተለያዩበት ጨዋታ የለም። አዳማ ከተማ አምስት በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ወላይታ ድቻ ቀሪዎቹን ሶስት ጨዋታዎች አሸንፏል። በግብ ማስቆጠሩም በኩል እንዲሁ ተመጣጣኝ ቁጥር ያላቸው ሲሆን አዳማ 10 እንዲሁም ድቻ 8 ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል።

– አዳማ ላይ የተጋናኙባቸው አራት ጨዋታዎች በሙሉ ባለሜዳው በአሸናፊነት ሲያጠናቀቁ ወላይታ ድቻ አዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም ማስቆጠር የቻለው አንድ ግብ ብቻ ነው።

– አዳማ ከተማ በሜዳው ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች አንድ ሽንፈት እና አንድ የአቻ ውጤት ቢገጥመውም የመጨረሻዎቹን አራቱን ጨዋታዎች በድል መወጣት ችሏል።

– እስካሁን ከሜዳቸው ውጪ ምንም ጨዋታ ማሸነፍ ያልቻሉት ወላይታ ድቻዎች ሁለት ጊዜ ነጥብ ተጋርተው ሲመለሱ አምስት ሽንፈቶች ገጥመዋቸዋል።

ዳኛ

– ጨዋታው በኢንተርናሽል ዳኛ አማኑኤል ኃይለሥላሴ የመሀል ዳኝነት ይመራል። ከዚህ ቀደም በአንድ የአዳማ ከተማ ጨዋታ ላይ የመዳኘት አጋጣሚ የነበረው አርቢትሩ እስካሁን በአራት ጨዋታዎች 19 የቢጫ ካርዶች እና ሁለት የፍፁም ቅጣት ምቶች ሰጥቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

አዳማ ከተማ (4-2-3-1)

ሮበርት ኦዶንካራ

ሱለይማን ሰሚድ – ምኞት ደበበ – ተስፋዬ በቀለ – ሱለይማን መሀመድ

አዲስ ህንፃ – ኢስማኤል ሳንጋሪ

ዐመለ ሚልኪያስ – ከነዓን ማርክነህ – በረከት ደስታ

ዳዋ ሆቴሳ

ወላይታ ድቻ (4-1-3-2)

መኳንንት አሸናፊ

እሸቱ መና – ዐወል አብደላ – ውብሸት ዓለማየሁ – ኄኖክ አርፌጮ

በረከት ወልዴ

ቸርነት ጉግሳ – አብዱልሰመድ ዓሊ – ዘላለም እያሱ

ሳምሶን ቆልቻ – ባዬ ገዛኸኝ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *