መቐለ መከላከያን በሚያስተናግድበት የ14ኛ ሳምንት ጨዋታ ላይ የሚነሱ ነጥቦችን እንደሚከተለው ቃኝተናቸዋል።
በተለያየ ወቅታዊ አቋም ላይ የሚገኙት መቐለ 70 እንደርታ እና መከላከያ ነገ 09፡00 ላይ በትግራይ ስታድየም ይገናኛሉ። አራት ተከታታይ ድሎችን ያስመዘገቡት መቐለዎች ከአራተኛው እስከ ስምንተኛው ሳምንት ታይቶባቸው የነበረውን መቀዘቃቀዝ ቀልብሰው ከሰንጠረዡ አጋማሽ ወደ ዋንጫው ፉክክር መምጣት ችለዋል። ከዚህ ፍፁም ተቃራኒ የሆነ ጉዞ ያደረጉት መከላከያዎች ደግሞ ድል አልባ የሆኑ ስድስት ሳምንታትን አሳልፈው ከሊጉ ወገብ ወርደው በወራጅ ቀጠና ውስጥ ለመገኘት ተገደዋል። አስር ጨዋታዎችን ብቻ ቢያደርጉም ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ የአራት ነጥቦች ልዩነት የተቀመጡት መቐለዎች መሪ የመሆን ተስፋቸው እንዳለ ነው። የነገው ጨዋታ ውጤትም ሁለት ደረጃዎችን የማሻሻል አጋጣሚን ሊፈጥርላቸው ይችላል። ወደ ድል መመለስ እጅግ የሚያስፈልጋቸው መከላከያዎችም ውጤት ከቀናቸው ለአንድ ሳምንት ከቆዩበት የወራጅ ቀጠና የመውጣት ዕድል አላቸው።
መቐለ 70 እንደርታ ጉዳት ላይ የሚገኙት ሦስቱ ተጫዋቾቹ አቼምፖንግ አሞስ ፣ አሸናፊ ሃፍቱ እና ሳሙኤል ሳሊሶ ያልተመለሱ ሲሆን መከላከያ ግን በቅጣትም ሆነ በጉዳት የሚያጣው ተጫዋች አይኖርም። ለረጅም ሳምንታት ጉዳት ላይ የሰነበተው አቤል ማሞ እና በቅርብ ጊዜያት ተጎድቶ ከቡድኑ ውጪ የነበረው አንበሉ ሽመልስ ተገኝም ከጉዳት መልስ ቡድናቸውን እንደሚያገለግሉ ይጠበቃል።
ግብ ጠባቂውን ጨምሮ በኋላ መስመሩ ላይ ተደጋጋሚ ስህተቶች ሲሰራ የሚስተዋለው መከላከያ የአቤል እና ሽመልስ መመለስ ይህን ችግሩን ሊያቃልልለት ቢችልም ሙሉ ለሙሉ ከስጋት ነፃ ይሆናል ለማለት ግን አያስደፍርም። የመቐለዎቹ አማኑኤል ገብረሚካኤል እና ያሬድ ከበደ ላይ ያነጣጠሩት የባለሜዳዎቹ ጥቃቶች ከጦሩ የተከላካይ መስመር ጀርባ ለመግባት የሚያስችል ፍጥነት እና መናበብን ያዳበሩ በመሆኑ የግብ ዕድሎችን መፍጠር የሚከብዳቸው አይመስልም። በተለይም በቡድኑ ውስጥ ያሉት የቦታዎቹ ተሰላፊዎች በሙሉ የተሞከሩበት የግራ እና ቀኝ የመከላከያ ተከላካይ ክፍል የመቐለዎች ኢላማ ሊሆን ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ መቐለዎች ከኋላ ያላቸው ወጥ የተጨዋቾች ምርጫ በቡድኑ የመከላከል አዱረጃጀት ውስጥ የፈጠራቸውን ጥምረቶች ለማለፍ በማጥቃቱ በኩል የነበረውን ጥንካሬ እያጣ ለመጣው መከላከያ ቀላል አይሆንም። ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ሳምንት ወደ ሜዳ የተመለሰው ተመስገን ገብረኪዳን ለወትሮው የሚያሳየው እንቅስቃሴ በግሉ በተከላካዮች መሀል ክፍተትን ሲፈጥር መታየቱ ግን ለጦሩ አማካዮች የቅብብል አማራጮችን ሊፈጥር ይችላል።
የእርስ በርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች
– መቐለዎች ወደ ሊጉ በመጡበት የ2010 የውድድር ዓመት የተገናኙባቸውን ሁለት ጨዋታዎች በተመሳሳይ የ1-0 ውጤቶች ተሸነንፈዋል። ሁለቱም ድሎቹን ያሳኩት በሜዳቸው ባደረጓቸው ጨዋታዎች ነበር።
– መቐለ 70 እንደርታ በትግራይ ስታድየም ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች አራት አሸንፎ በአንዱ ነጥብ ተጋርቷል።
– ካሉት አስር ነጥቦች ግማሹን ከሜዳው ውጪ ያገኘው መከላከያ ከአዲስ አበባ ስታድየም ወጥቶ አራት ጨዋታዎችን ሲያደርግ ሽንፈት የገጠመው በመጨረሻው የሲዳማ ጨዋታ ብቻ ነበር።
ዳኛ
– ጨዋታው ለማኑኄ ወልደፃዲቅ አራተኛው የሊግ ጨዋታ ሲሆን እስካሁን በዳኘባቸው ጨዋታዎች 13 የቢጫ ካርዶችን እና ሁለት የፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔዎችን አሳልፏል።
ግምታዊ አሰላለፍ
መቐለ 70 እንደርታ (4-2-3-1)
ፍሊፔ ኦቮኖ
ስዩም ተስፋዬ – አሌክስ ተሰማ – አሚኑ ነስሩ – አንተነህ ገብረክርስቶስ
ጋብርኤል አህመድ – ሚካኤል ደስታ
አማኑኤል ገብረሚካኤል – ሐይደር ሸረፋ – ዮናስ ገረመው
ያሬድ ከበደ
መከላከያ (4-4-2 ዳይመንድ)
አቤል ማሞ
ሽመልስ ተገኝ – አዲሱ ተስፋዬ – አበበ ጥላሁን – ታፈሰ ሰረካ
ቴዎድሮስ ታፈሰ
ሳሙኤል ታዬ – ፍሬው ሰለሞን
ዳዊት እስጢፋኖስ
ተመስገን ገብረኪዳን – ምንይሉ ወንድሙ
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ–ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡