ሪፖርት | አማኑኤል ገብረሚካኤል ደምቆ በዋለበት ጨዋታ መቐለ 70 እንደርታ መከላከያን አሸነፈ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ዛሬ ከተደረጉት ጨዋታዎች መካከል ከፍተኛ ጎል የተስተናገደበት የመቐለ 70 እንደርታ እና መከላከያ ጨዋታ በመቐለ 5-2 አሸናፊነት ተጠናቋል። አማኑኤል ገብረሚካኤልም አራቱን ጎሎች በማስቆጠር ደምቆ ውሏል።

ባለሜዳዎቹ መቐለዎች ባለፈው ሳምንት ደቡብ ፖሊስን ካሸነፈው ስብስባቸው ቢያድግልኝ ኤልያስን አስወጥተው በሥዩም ተስፋዬ ሲተኩ መከላከያዎች በበኩላቸው ባለፈው ሳምንት ከሀዋሳ ከተማ አቻ ከተለያየው ስብስባቸው ሙሉቀን ደሳለኝ እና ሳሙኤል ታዬን በአማኑኤል ተሾመ እና ዳዊት እስቲፋኖስ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ሰባት ግቦች በተስተናገዱበት ጨዋታ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች እንግዶቹ መከላከያዎች የተሻለ ሲንቀሳቀሱ ሁለት ንፁህ የግብ ዕድሎችም አምክነዋል። ምንይሉ ወንድሙ ከፍሬው ሰለሞን የተቀበለው ኳስ የአሚን ነስሩን ስህተት ተጠቅሞ አክርሮ መትቶ ፍሊፕ ኦቮኖ በሚያስደንቅ ብቃት ወደ ውጭ ያወጣው ሙከራ ጦሮቹን መሪ ለማድረግ የተቃረበ ነበር። መከላከያዎች በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች መቐለዎች ኳስ እንዳይመሰርቱ ወደ ሳጥን ተጠግተው ፤ እንዲሁም የተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾች የቅብብል መስመር በመዝጋት ጥሩ ቢንቀሳቀሱም እንቅስቃሴው ከመጀመሪያዎቹ ሃያ ደቂቃዎች ያለፈ አልነበረም። በዚህም ቡድኑ ቴዎድሮስ ታፈሰ ከቅጣት ምት እንዲሁም ፍሬው ሰለሞን የሥዩም ተስፋዬን ስህተት ተጠቅሞ ካደረገው ሙከራ ውጭ ይህ ነው የሚባል ንፁህ ዕድል መፍጠር አልቻለም።

በዚ መሐል ምንይሉ ወንድሙ በሃያ ሰባተኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት እስጢፋኖስ በግሩም ሁኔታ ያሻማለትን ቅጣት ምት በግንባሩ በመግጨት ጎል አስቆጥሮ መከላከያዎችን መሪ ማድረግ ችሏል ። ሆኖም የመከላከያ መሪነት የቆየው ለአንድ ደቂቃ ብቻ ነበር። ያሬድ ከበደ በመከላከያ ሳጥን ውስጥ በተሰራበትን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት አማኑኤል ገብረሚካኤል አስቆጥሮ መቐለዎችን አቻ ማድረግ ችሏል።

በጨዋታው የተለመደው ፈጣን የማጥቅት ሽግግር ማሳካት ያልቻሉት መቐለዎች ምንም እንኳ ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ባይደርሱም ቡድኑ ባገኛቸው ጥቂት ዕድሎች በሶስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ እጅግ ውጤታማ ነበር። ከዚ በተጨማሪም ባለሜዳዎቹ ግብ ከተቆጠረበት በኋላ መረጋጋት ያቃተው የመከላከያን የተከላካይ ክፍል በሚሰሯቸው ቀላል ግለሰባዊ ጥፋቶች ተጠቅመው የግብ ዕድሎች ፈጥረው ነበር። በተለይም አማኑኤል ገ/ሚካኤል የተከላካዮች ስህተት ተጠቅሞ ይዞ ገብቶ ግብ ጠባቂ ጭምር አታሎ በማለፍ ያመከነው የግብ ዕድል ይጠቀሳል።

በመጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ወደ ተሻለ ቅርፅ የመጡት መቐለዎች በሰላሳ ሰባተኛው ደቂቃ ያሬድ ከበደ ባስቆጠራት ግብ መሪ መሆን ችለዋል። ሐይደር ሸረፋ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ከመስመር ያሻገረለትን ኳስ መትቶ በተከላካዮች ሲመለስ በቅርብ ርቀት የነበረው ያሬድ ከበደ አስቆጥሮ ነበር መቐለዎች መርተው ወደ ዕረፍት እንዲያመሩ ያስቻለው።

የባለሜዳዎቹ መቐለዎች ሙሉ ብልጫ እንዲሁም የመከላከያ ደካማ የመከላከል አደረጃጀት የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ በአንፃራዊነት ጥሩ የኳስ ፍሰት የተስተዋለበት ነበር። ከዚ ውጪ በሁለተኛው አጋማሽ የተከላካይ ክፍላቸውን ወደ መሐል ሜዳ በእጅጉ አስጠግተው ሲከላከሉ የታዩት መከላከያዎች አጨዋወቱ ተጋጣሚን በሜዳው ለማፈን እንዲሁም ቡድኑ ከኳስ ውጭ ብዙ ጉልበት እንዳያባክን ቢረዳውም ከተከላካይ ጀርባ የተተወውን ክፍት ቦታ ለመቐለዋች በተለይም ለያሬድ ከበደ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል ሲሳይ ሲሆን ነበር፤ በተለይም አማኑኤል ያመከናቸው ሶስት ንፁህ የግብ ዕድሎች ለዚ ማሳያ ናቸው።

ሥዩም ተስፋዬ ባደረገው ሙከራ ጥቃታቸው የጀመሩት ባለሜዳዎቹ ግብ ለማስቆጠር ብዙም ደቂቃ አልፈጀባቸውም። በ51ኛው ደቂቃ ላይ ዮናስ ገረመው ያሻማው የማዕዘን ምት ያሬድ ከበደ ሲመታው በግቡ አፋፍ የነበረው አማኑኤል ገ/ሚካኤል ጨርፎ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል፤ ከሶስት ደቂቃ በኋላም አማኑኤል ከራሳቸው የግብ ክልል ሥዩም በግሩም ሁኔታ ያሻገረለትን ኳስ በአግባቡ ተቆጣጥሮ ከግብጠባቂው በላይ መትቶ በማስቆጠር ሐት-ትሪክ ሰርቷል።

 

በሁለተኛው አጋማሽ እጅግ ወርደው የታዩት መከላከያዎች ዳዊት እስጢፋኖስ ከቅጣት ምት ካደረገው ግሩም ሙከራ ውጭ ይህ ነው የሚባል ዕድል መፍጠር አልቻሉም። በአንፃሩ መቐለዎች ተደደጋጋሚ ግዜ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ተጠግተው በርካታ ዕድሎች ፈጥረዋል። አማኑኤል ከይድነቃቸው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ግብጠባቂው በድንቅ ብቃት ያዳነው እና ራሱ አማኑኤል ከቅጣት ምት መትቶ አግዳሚው ገጭቶ የወጣው ሙከራ ለግብ የቀረቡ ነበሩ።

በ84ኛው ደቂቃ መከላከያ ሳጥን ላይ በተሰራው ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት አማኑኤል ገብረሚካኤል አስቆጥሮ በጨዋታው ለቡድኑ አምስተኛ ለሱ ደግሞ አራተኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል። በሰማንያ ሰባተኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በመቐለ ሳጥን ኳስ በእጅ በመነካቱ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ምንይሉ ወንድሙ አስቆጥሮ ጨዋታው በመቐለ 70 እንደርታ 5-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በማኑሄ ወልደፃድቅ ጥሩ ብቃት የተመራው ጨዋታው ምንም ካርድ ያልመተዘገበበት ሆኖ ያለፈ ሲሆን ድሉን ተከትሎ መቐለ 70 እንደርታ አምስተኛ ተከታታይ ድሉን ሲያስመዘግብ በመጥፎ አቋም ላይ የሚገኘው መከላከያ በውድድር ዓመቱ ለሦስተኛ ጊዜ በአንድ ጨዋታ አምስት ጎሎችን አስተናግደዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *