በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛው ሳምንት ዛሬ ሀዋሳ ላይ ሲዳማ ቡና ደደቢትን 3-0 በሆነ ውጤት ካሸነፈ በኃላ የሁለቱ ክለብ አሰልጣኞች ለሶከር ኢትዮጵያ የሚከተለው አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
“የቡድናችንን ጥንካሬ ያየንበት ጨዋታ ነበር” ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና
ስለ አጀማመራቸው መቀዝቀዝ
ምናልባት እነሱ ሲጀምሩ ኳሱን ስላንሸራሸሩ የተሻሉ ይምሰሉ እንጂ በኔ እምነት አልነበሩም። ራሳችን ነው የፈቀድንላቸው፤ በዚህም ዙሪያ ተነጋግረናል፡፡ እነሱ ይህን እንደሚያደርጉ እናውቅ ነበርና፡፡ ያን ስላወቅንም ነው ክፍተት የፈጠርነው፡፡ ከዛ በኋላ ግብ ልናገባ የቻልነውም የተነጋገርነውን በማድረጋችን ነው፡፡ ከዛ ባለው ሙሉ ደቂቃ ቡድናችን ኳስ ይዞ ነው የተጫወተው፡፡ የተሻለ እንቅስቃሴንም አድርገን ነው ጎሎችን ያገባነው። እነሱ አስቸጋሪ ዕድልን ፈጥረው ግብ ጠባቂያችንን አልፈተኑም፡፡ የቡድናችንን ጥንካሬ ያየንበት ነበር፤ ይህ የሆነው ግን ደደቢት ጥሩ ሳይሆን የመጣ አይደለም፡፡ ደደቢት ብዙ ቡድኖችን እየፈተነ ያለ ክለብ ነው፡፡
የሚሊዮን ሰለሞን ልዩነት ፈጣሪ መሆን
ለሚሊዮን ነፃ ሚና ነበር የሰጠነው፡፡ ምክንያቱም የደደቢት አጨዋወት ምን እንደሆነ ስለምናውቅ፡፡ ነፃነት የሰጠነው ደግሞ የነሱ የመስመር ተጫዋቾች ወደ ውስጥ ገብተው ስለሚጫወቱ በሱ በኩል የነበረው የመጫወቻ ቦታ ደግሞ ክፍት ነበር፡፡ ያንን ለመጠቀም አስበን ነበር፡፡ እሱም በሚገባ ተጠቅሞታል፡፡ ቶሎ ቶሎም ግብ ጋር ይደርስ የነበረው ለዛ ነው፡፡ ብዙ ነገርም መስራት ይችላል፤ አቅም አለው፡፡ ያ እምነቱም ስላለ ነው፡፡
” የሲዳማ ቡና የበላይነት እንጂ የኛ ድክመት አልነበረም ይህ ውጤት እንዲመዘገብ ያደረገው ” ይድነቃቸው አለሙ – ደደቢት
ስለ ጨዋታው
ሲዳማ ቡና ጠንካራ ቡድን ነው፡፡ ደደቢት ደግሞ በፊት ከነበረው ከነበረው ስብስቡ በወጣቶች የተመረኮዘ ቡድን ነው፡፡ ሲዳማ ቡና በጣም ልምድ ባላቸው የተገነባ ጥሩ ኳስን የሚጫወት እና ጠንካራ ነው፡፡ በመስመር ለሚመጡብን ኳሶች በጣም ነበር ጥንቃቄ ያደረግነው፡፡ እናም እንደፈራነው የመጀመሪያዋም ግብ በመስመር ተቆጥራብናለች፡፡ ሁለተኛዋ ከገባች በኋላ ደግሞ ትልቅ የስነልቦና ችግር ታይቷል፡፡ ወደ አሸናፊነትም ለመግባት በተመሳሳይ በተጫዋቾቹ ላይ ብዙ የመጓጓት ነገሮች ይታይባቸዋል እንጂ ወደፊት የኢትዮጵያ ኳስ ሊቆጣጠሩ የሚችሉ ተጫዋቾች አሉን። ዛሬ ሜዳውም ተፅእኖ ነበረው፤ ጉልበት የሚፈልግ ሜዳ ነው። የኛ ተጫዋቾችም ተቋቁሞ ለመውጣት ከልምድ አንፃር በጣም ክፍተት ታይቶብናል። ግን የሲዳማ ቡና የበላይነት እንጂ የኛ ድክመት አልነበረም ይህ ውጤት እንዲመዘገብ ያደረገው።