ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | የ14ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

ትናንት ስድስት ጨዋታዎች የተስተናገዱበት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በሁለት ጨዋታዎች ይቀጥላል። ሀዋሳ እና አዲስ አበባ ላይ ስለሚደረጉት እነዚህ ጨዋታዎች ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል። 

ሀዋሳ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

ረፋድ 09፡00 ላይ በሀዋሳው ሰው ሰራሽ ሜዳ ሀዋሳ ከተማ ባሳለፍነው ሳምንት በሜዳው ሲዳማ ቡናን ያስተናግድ የነበረበት ጨዋታ በፀጥታ ችግር ምክንያት የተላለፈበት ድሬዳዋ ከተማን ያስተናግዳል። እስካሁን በርካታ ግቦች (21) በማስቆጠር በሊጉ ቀዳሚ የሆነው ሀዋሳ ከተማ ከመከላከያ ጋር አቻ ተለያይቶ ወደ ሁለተኝነት ከፍ የማለት ዕድሉን ቢያሳልፍም አሁንም በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ካሉ ቡድኖች መካከል ይገኛል። አስር ጨዋታዎች ያደረገው ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ ከመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎቹ ግብ ማስቆጠር ሳይችል አንድ ነጥብ ብቻ አሳክቶ በአጠቃላይም በአማካይ በጨዋታ አንድ ነጥብ በመሰብሰብ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በመሆኑም ከዛሬው ጨዋታ የሚገኙት ነጥቦች ሀዋሳ ከተማን ወደ አንደኝነት ወይንም ሁለተኛነት ከፍ በማለት በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ያለውን ቦታ አስጠብቆ እንዲቀጥል የማስቻላቸውን ያህል ድሬዳዋ ከተማንም ከአደጋው ዞን ፈቀቅ እንዲል የሚያግዙት በመሆናቸው ወሳኝነታቸው የጎላ ይሆናል። 

የመስመር ተመላላሾቹ ደስታ ዮሀንስ እና ዳንኤል ደርቤ ከጉዳት የተመለሱለት ሀዋሳ ከተማ ብሩክ በየነ ብቻ ለጨዋታው ብቁ የመሆኑ ነገር ከማጠራጠሩ በቀር ቀሪው ስብስቡ በሙሉ ጤንነት ላይ ይገኛል። በድሬዳዋ በኩልም ጉዳት ላይ የሰነበተው ራምኬል ሎክ ወደ ሜዳ እንደሚመለስ ሲጠበቅ ፍቃዱ ደነቀ በመጠነኛ የጡንቻ ጉዳት ረመዳን ናስር ደግሞ የጋብቻ ሥነ ስርዓቱን የሚከውን በመሆኑ ወደ ሀዋሳ አልተጓዙም።

የእርስ በርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ 14 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን በእኩል 4 አጋጣሚዎች ተሸናንፈው 6 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። በ14ቱ ጨዋታዎች ድሬዳዋ ከተማ 15 ሀዋሳ ከተማ 13 ግቦችን አስቆጥረዋል።

– ሀዋሳ ላይ ካደረጓቸው ስምንት ጨዋታዎች ውስጥ ስድስቱን በድል የተወጣው ሀዋሳ ከተማ ሁለት ሽንፈቶች ሲገጥመው በሜዳው ነጥብ የተጋራበት ጨዋታ ግን የለም።

–  እስካሁን ከሜዳው ውጪ ድል ያልቀናው ድሬዳዋ ከተማ ከአምስት ጨዋታዎች በሦስቱ የአቻ ውጤቶችን ሲያስመዘግብ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል።

                                            
ዳኛ

– በአምስት ጨዋታዎች 14 የቢጫ ካርዶችን የመዘዘው ወልዴ ንዳው ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት የመምራት ኃላፊነት ተሰጥቶታል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዋሳ ከተማ ( 4-2-3-1) 

ሶሆሆ ሜንሳህ 

 አዲስዓለም ተስፋዬ – ላውረንስ ላርቴ – መሣይ ጳውሎስ – ያኦ ኦሊቨር

አስጨናቂ ሉቃስ –ኄኖክ ድልቢ

ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን – ታፈሰ ሰለሞን – አዳነ ግርማ

እስራኤል እሸቱ

ድሬዳዋ ከተማ (4-4-2)

ሳምሶን አሰፋ

ገናናው ረጋሳ – አንተነህ ተስፋዬ – በረከት ሳሙኤል – ሳሙኤል ዮሃንስ

ሚኪያስ ግርማ – ፍሬድ ሙሺንዲ –  ምንያህል ይመር – ረመዳን ናስር

ሐብታሙ ወልዴ – ኃይሌ እሸቱ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ፋሲል ከነማ

ከትናንት ጨዋታዎች በኋላም በሊጉ አናት መቆየት የቻለው ቅዱስ ጊዮርጊስ ዛሬ 10፡00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም በዚህ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ መዲናዋ የሚመጣው ፋሲል ከነማን ያስተናግዳል። ጨዋታው ቡድኖቹ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ የሚገኙ እንደመሆናቸው ከፍ ያለ ግምት የተሰጠውም ነው።  ከዚህ ባለፈ ቅዱስ ጊዮርጊስ በስምንተኛው ሳምንት ፋሲል ከነማ ደግሞ በአራተኛው ሳምንት ኢትዮጵያ ቡናን ከገጠሙ በኋላ ባደረጓቸው ጨዋታዎች ከስድስተኛ ደረጃ በላይ ያሉ ክለቦችን ባለማግኘታቸው ዛሬ የውድድር ጉዟቸውን የሚፈትን ፍልሚያ እንደሚጠብቃቸውም ይታመናል። ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሙሉ 15 ነጥቦችን በሰበሰቡባቸው የመጨረሻ አምስት ጨዋታዎቻቸው አንድ ግብ ብቻ ማስተናገዳቸው ሌላኛው ጥንካሪያቸው ሆኗል። ፋሲል ከነማም ምንም እንኳን የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎቹን ያለግብ ቢያጠናቅቅም ተስተካካይ ጨዋታዎቹን ከግምት ባስገባ ስሌት ወደ ሊጉ አናት የመድረስ ተስፋው አሁንም በእጁ ይገኛል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ የረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የሚገኘው መሀሪ መናን ጨምሮ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ጉዳት ገጥሟቸው ተቀይረው ለመውጣት የተገደዱት  ሳልሀዲን በርጌቾ እና ጌታነህ ከበደን በዛሬው ጨዋታ አይጠቀምም። ላለፉት ጥቂት ሳምንታት ጉዳት ላይ ከነበሩት ተጫዋቾች መካከል ደግሞ አሜ መሀመድ ወደ ሜዳ እንደሚመለስ ሲጠበቅ የአብዱልከሪም መሀመድ ጉዳይ ግን አለየለትም። በፋሲል ከተማ በኩል ደግሞ ከጉዳት የተመለሱ ተጨዋቾች ተበራክተዋል። በዚህም መሰረት ሱራፌል ዳኛቸው ፣ ኤፍሬም አለሙ ፣ ሀብታሙ ተከስተ ፣ ሰይድ ሁሴን ፣ ያስር ሙገርዋ ፣ በዛብህ መለዮ እና ዮሴፍ ዳሙዬ ወደ ሜዳ ሲመለሱ ፋሲል አስማማው እና ሙጂብ ቃሲም ግን አሁንም  ከጉዳታቸው አላገገሙም ።

የእርስ በርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– ሁለቱ ክለቦች በአምስት የሊግ ጨዋታዎች ሲገናኙ ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ የፎርፌ ውጤትን ጨምሮ ሦስት ድሎችን ሲያስመዘግብ ፋሲል አንዴ ድል የቀናው ሲሆን በአንድ አጋጣሚ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። በግንኙነታቸው ወቅት ከተቆጠሩ 13 ግቦች ውስጥ ቅዱስ ጊዮርጊስ የ8ቱ ፋሲል ከተማ ደግሞ የ5ቱ ባለቤቶች ናቸው።

– ቅዱስ ጊዮርጊስ በሜዳው ሰባት ጨዋታዎችን አድርጎ በመጀመሪያው ጨዋታ ሽንፈት ሲገጥመው በመቀጠል አራት ድሎችን ሲያስመዘግብ ሁለት ጊዜ አቻ ተለያይቷል።

– ፋሲል ከነማ ከሜዳው ከወጣባቸው አምስት ጨዋታዎች ሁለት ድል አስመዝግቦ ሁለቴ ነጥብ ሲጋራ በአንድ ጨዋታ ሽንፈት ገጥሞታል።

ዳኛ

– ኢንተርናሽናል ዳኛ ብሩክ የማነ ብርሀን ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት ይመራዋል። አርቢትሩ እስካሁን ሁለቱን ክለቦች አንድ አንድ ጊዜ የዳኘ ሲሆን በአራት ጨዋታዎች 16 የቢጫ ካርዶች እና አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥቷል። 

ግምታዊ አሰላለፍ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (3-5-2)

ፓትሪክ ማታሲ

አስቻለው ታመነ  – ምንተስኖት አዳነ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ 

በኃይሉ አሰፋ – ሙሉዓለም መስፍን – ናትናኤል ዘለቀ – ኄኖክ አዱኛ

ታደለ መንገሻ

ሳላሀዲን ሰዒድ – አቤል ያለው

ፋሲል ከነማ (4-3-3)

ሚኬል ሳማኬ     

ሰዒድ ሁሴን – ያሬድ ባየህ – ከድር ኩሊባሊ – አምሳሉ ጥላሁን

ሰለሞን ሀብቴ – ሐብታሙ ተከስተ – ሱራፌል ዳኛቸው

ሽመክት ጉግሳ – ኤዲ ቤንጃሚን – አብዱራህማን ሙባረክ

              

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *