ሪፖርት | ፋሲል የጊዮርጊስን ተከታታይ አሸናፊነት በመግታት ነጥብ ተጋርቷል

14ኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ፋሲል ከነማ ተገናኝተው ባለሜዳዎቹ ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ነጥብ የጣሉበትን እንግዶቹ ደግሞ ለሦስተኛ ተከታታይ ጊዜ ነጥብ የተጋሩበትን የ 1-1 ውጤት አስመዝግበዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ወልዋሎ ዓ /ዩን ከረታበት የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ጉዳት የገጠመው ጌታነህ ከበደን ብቻ በአቤል ያለው በመተካት ለዛሬው ጨዋታ ቀርቧል። አማካይ ክፍል ላይ ከጉዳት የተመለሱት ኤፍሬም አለሙ እና ሱራፌል ዳኛቸውን በሠለሞን ሀብቴ እና መጣባቸው ሙሉ ምትክ በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ያካተቱት ፋሲል ከነማዎች ደግሞ በዓለምብርሀን ይግዛው እና ኤድ ቤንጃሚን ምትክም አብዱርሀማን ሙባረክ እና ኢዙ አዙካን በማስገባት ከአዳማ ያለ ግብ ከተለያዩበት ጨዋታ የአራት ተጨዋቾች ለውጥ አድርገዋል።

ጨዋታው ከተሰጠው ግምት በተለየ በተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ የጀመረ ሲሆን 8ኛው ደቂቃ ላይ ሳላዲን ሰዒድ ከሳጥን ውጪ ካደረገው ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ውጪ ግብ እስከተቆጠረበት ጊዜ ድረስ በመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ ተወስኖ የቆየ ነበር። ኳስ ተቆጣጥረው ለመጫወት የሚሞክሩት ፋሲል ከነማዎች ወደ ተጋጣሚያቸው ሳጥን በተሻለ የቀረቡት አልፎ አልፎ ከሱራፌል ዳኛቸው በሚነሱ ረዘም ያሉ ኳሶች ነበር። በተመሳሳይ ግልፅ የማግባት አጋጣሚ መፍጠር ያልቻሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶችም የተሻለ ቀጥተኛነት ቢታይባቸውም መሀል ላይ ከሚቀሟቸው ኳሶች ወደ ሁለቱ አጥቂዎቻቸው በሚያደርሷቸው ኳሶች ነበር አጋጣሚ ለመፍጠር የሚሞክሩት። ነገር ግን ሁለቱም ቡድኖች በመረጧቸው መንገዶች ቶሎ ቶሎ ከሚቆራረጡ ቅብብሎች ውጪ በወጥነት ጫና መፍጠር አልቻሉም።

የጨዋታው ሙከራ አልባነት 20ኛውን ደቂቃ ካለፈ ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ፋሲል ከነማዎች ያገኙትን አጋጣሚ ወደ መጀመሪያ ሙከራነት ቀይረው ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ከሙሉዓለም መስፍን ባስጣሉት ኳስ ሦስት ለሁለት ሆነው ወደ ጊዮርጊስ ሜዳ ከገቡ በኋላ አብዱርሀማን ሙባረክ ከኤፍሬም አለሙ የደረሰውን ኳስ ከአስቻለው ታመነ ጋር ታግሎ በማታሲ አናት ላይ በማሳለፍ ድንቅ ግብ አስቆጥሯል። ሆኖም የመስመር አጥቂው ግቧን ካስቆጠረ በኋላ ባስተናገደው ጉዳት በሜዳ ላይ መቆየት የቻለው ለ 14 ደቂቃዎች ነበር። በመጨረሻም በሰለሞን ሀብቴ ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል።

ግብ ካስተናገዱ በኋላ የመስመር ተመላላሾቻቸውን አቅጣጫ በመቀያየር ኄኖክ አዱኛን ወደ ግራ በኃይሉ አሰፋን ደግሞ ወደ ቀኝ ያመጡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ተሻጋሪ ኳሶችን ወደ ሳጥን ውስጥ በመጣል ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል። ሆኖም በተደጋጋሚ የቅብብል ስህተቶችን ይሰሩ የነበረ መሆኑን ተከትሎ በራሳቸው ሜዳ ላይ የቀሩት ፋሲሎችን ማለፍ ተስኗቸዋል። 30ኛው ደቂቃ ላይ ብቻ በኃይሉ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ከድር ኩሊባሊ ሲያወጣው አግኝቶ አቤል ያለው አክርሮ ሞክሮ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶበታል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከዕረፍት በፊት አቻ የሆነበትን ግብ ሲያገኝም ግቡ በሙሉዓለም የግል ጥረት የተገኘ ነበር። ጥሩ ጨዋታ ያሳለፈው የተከላካይ አማካዩ 41ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር ከፋሲል አማካዮች ጋር ታግሎ ያገኘውን ኳስ አሻማ ተብሎ ሲጠበቅ በቀጥታ አክርሮ በመምታት ነበር ያስቆጠረው። ዳግም መሪ ለመሆን ወደ ፊት ገፍተው የተጫወቱት ፋሲሎችም 45ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ አጋጣሚ ፈጥረው ነበር። በዚህም ቅፅበት ኤፍሬም ኢዙ አዙካን በተከላካዮች መሀል በሰነጠቀው ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር ቢያገናኘውም ናይጄሪያዊው አጥቂ ለውሳኔ በመዘግየቱ የጊዮርጊስ ተከላካዮች ደርሰው አስጥለውታል።


ከእረፍት መልስ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተሻለ መልኩ ጫና ፈጥረው በመጫወት ጀምረዋል። በአንፃሩ አፄዎቹ ከኳስ ውጪ በብዛት ሜዳቸው ላይ በመቆየት ኳስ ሲነጥቁ ደግሞ በአጫጭር ቅብብሎቻቸው በመታገዝ ወደ ፊት ለመሄድ ሲሞክሩ ይታይ ነበር። ሆኖም የፋሲሎች የማጥቃት ሽግግር ፍጥነት ዝግ በማለቱ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ከመድረሳቸው በፊት ቅብብሎቻቸው በጊዮርጊስ የኋላ መስመር ሲቋረጥባቸው ይታይ ነበር። 65ኛው ደቂቃ ላይ ኢዙ አዙካ ወደ መስመር ወጥቶ ከሽመክት ጉግሳ የተቀበላውን ኳስ ሳጥን ውስጥ ለነበረው ሰለሞን ለማድረስ ተቃርቦ ተከላካዮች ያወጡበት አጋጣሚም ቡድኑ በተሻለ ወደ ሳጥን የገባበት የጨዋታ ሂደት ነበር።


የግብ ሙከራ በማድረግ የተሻሉ በነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በኩል 56ኛው ደቂቃ ላይ ከበኃይሉ የደረሰውን ኳስ ወደ ፋሲል ሳጥን መግቢያ ላይ የተቆጣጠረው አቤል ሞክሮ ለጥቂት በግቡ አግዳሚ ሲወጣበት 61ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ኄኖክ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታውን ሞክሮ ተተከላካዮች ተደርበው አክሽፈውበታል። 70ኛው ደቂቃ ላይ አሜ መሀመድን በታደለ ቀይረው ያስገቡት ጊዮርጊሶች ራሳቸውን ለተሻጋሪ ኳሶች ይበልጥ ዝግጁ ሲያደርጉ 73ኛው ደቂቃ ላይ ሳላዲን ከግራ ያሻማውን በኃይሉ ሳጥን ውስጥ ሞክሮ ሳማኬ ሲያድንበት በዚሁ ደቂቃ አቤል ካሾለከለት ኳስ ናትናኤል ዘለቀ ያደረገው ሙከራ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጨዋታው የተሻለ ክፍተት ታይቶበት ቡድኖቹ በቶሎ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ሲቀርቡ ቢታይም ንፁህ የግብ አጋጣሚን ግን አልተመለከትንም። ከኤሜ በተጨማሪ አበበከር ሳኒንም ያስገቡት ጊዮርጊሶች ከግራ በሚነሱት ኳሶቻቸው ደስተኛ ባለመሆናቸው ኄኖክን በሳሙኤል ተስፋዬ ቢቀይሩም ይህ ችግራቸውን መቅረፍ አልተቻላቸውም። ፋሲሎችም ወጣቱን የመስመር አጥቂ ዓለምብርሀን ይግዛው እና ኤድ ቤንጃሚንን ቢያስገቡም ወደ ፊት ሲሄዱ የሚኖራቸውን ፍጥነት ማስተካከል አልቻሉም። ወደ መጨረሻ ደቂቃ ላይ ከቁጥር ብልጫ ጋር ያገኙትን የመልሶ ማጥቃት ዕድልም መጠቅም ሳይችሉ ጨዋታው ፍፃሜውን አግኝቷል።

በውጤቱም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአምስት ተከታታይ ድሎች በኋላ ነጥብ ቢጥልም አንደኛነቱን ሲያስጠብቅ ሦስተኛ ተከታታይ የአቻ ውጤት ያስመዘገቡት ፋሲሎች ደግሞ 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *