የ5ኛ ሳምንት የ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ምድብ ለ ጨዋታዎች ትላንት እና ዛሬ ሲደረጉ ኢትዮጵያ መድን፣ አፍሮ ፅዮን እና ፋሲል ከነማ ድል አስመዝግበዋል።
ጎንደር ላይ ኤሌክትሪክን ያስተናገደው ፋሲል ከነማ 1-0 በማሸነፍ ባለፈው ሳምንት በአዳማ ከነማ ከደረሰበት የ 5-1 ሽንፈት አገግሟል። በመጀመሪያው አጋማሽ ተጭነው የተጫወቱት የፋሲሎች በተደጋጋሚ ወደግብ መድረስ ቢችሉም ግብ ማግኝት አልቻሉም ነበር። የተሻለ የመሐል ሜዳ ፉክክር በታየበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የፋሲል ከነማ የማጥቃት እንቅስቃሴ በቀኝ መስመር ያዘነበለ ነበር።
በሙከራ ደረጃ ከናትናኤል ገ/ሚካኤል በቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ያሬድ አበበ ከሳጥን ውስጥ ወደግብ አክርሮ መትቶ የግብ አግዳሚ የመለሰበት የሚጠቀስ ነበር። 21ኛ ደቂቃ ላይ ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ በቀኝ መስመር ይዞት የገባዉን ኳስ መሬት ለመሬት ያሻገረለትን ኳስ የሽዋስ በልሁ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ግሩም ግብ በማስቆጠር ፋሲል ከነማን መሪ አድርጓል። ከተቆጠረባቸው በኋላ አጥቅተው ለመጫወት የሞከሩት እንግዳዎቹ ከቆሙ ኳሶች በፀጋ ደርቤ እና አደም አባስ ጥሩ ሙከራዎች ቢያደርጉም ግብ ማግኝት ሳይችሉ ነበር ወደ እረፍት ያመሩት።
ሁለተኛው አጋማሽ ላይ የተሻለ ለመንቀሳቀስ ጥረት ሲያደርጉ የተስተዋሉት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ናትናኤል አብርሃ ከማዕዘን የተሻማን ኳስ በጭንቅላቱ ገጭቶ ግብ ጠባቂ ያዳነበት የሚያስቆጭ ኳስ ነበር። ተቀይሮ የገባው እስራኤል ገ/መስቀል ከቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ መትቶ ግብ ጠባቂ ያዳነበትም ሌላው ተጠቃሽ ሙከራ ነበር።
በፋሲል ከነማ በኩል በሁለተኛው አጋማሽ የመሀል ሜዳ የኳስ ቁጥጥሩን ተመጣጣኝ ለማድረግ ጥረት ሲያደርጉ የተስተዋለ ሲሆን የመስመር ተከላካዩ ሙሉቀን አዳሙ እና የመስመር አጥቂው የሽዋስ በልሁ ተጎድተዉ በመዉጣታቸዉ ቡድኑ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ቅርፅ ማጣት ተስተውሎበታል። በሙከራ ደረጃ ናትናኤል ማስረሻ ግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ያመከነዉ ኳስ በሁለተኛው አጋማሽ የሚስቆጭ አጋጣሚ ነበር። በፋሲል ከነማ በኩል እንዲሁም ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ በቀኝ መስመር ይዞ ገብቶ ወደግብ አክርሮ የመታው የሚጠቀሱ ሙከራዎች ነበሩ።
ቅዳሜ መድን ሜዳ ላይ ወልቂጤ ከተማን የገጠመው ኢትዮጵያ መድን 7-1 በማሸነፍ የውድድር ዘመኑን ከፍተኛ ድል አስመዝግቧል። ባሳለፍነው ሳምንት በሜዳው በአሰላ ኅብረት 5-2 የተረታው ወልቂጤ ከተማ በዚህም ሳምንት በርካታ ጎል ተቆጥሮበታል።
አፍሮ ፅዮን 24 ሜዳ ላይ አዲስ አበባ ከተማን ገጥሞ 1-0 ማሸነፍ ቸሏል። ከመጀመርያው ሳምንት ድል በኋላ ተከታታይ ሶስት ጨዋታዎች አቻ የተለያየው አፍሮ ፅዮን ወደ ድል መመለሱን ተከትሎ ከመሪው ጋር በነጥብ ተስተካክሏል።
ሀላባ ላይ ሀላባ ከተማ ከ አዳማ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ 2-2 ተጠናቋል። አዳማ ነጥብ ጥሎ ቢወጣም ከአፍሮ ፅዮን በግብ ልዩነት በልጦ ሰንጠረዡን መምራት ቀጥሏል።
– አሰላ ኅብረት በዚህ ሳምንት አራፊ ቡድን ነው።