በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሐ ተመድቦ እየተወዳዳረ የሚገኘው ጅማ አባቡና ከአሰልጠኝ መኮንን ማሞ ጋር ተለያይቷል፡፡
በድጋሚ ከተመሰረተ በለላ በጥቂት ዓመት ተሳትፎ በ2009 ወደ ፕሪምየር ሊጉ አድጎ የነበረውና አምና በከፍተኛ ሊጉ እስከመጨረሻው ጨዋታ ድረስ ተፎካካሪ የነበረው ጅማ አባቡና ዘንድሮ የውድድር ዘመኑን ዘግየት ብሎ ጥቅምት ወር አጋማሽ ዝግጅት ሲጀምር ቡድኑን ተረክበው በዋና አሰልጣኝነት እዲመሩ የቀድሞው የደብረብርሃን፣ ፊንጫ ስኳር፣ ሻሸመኔ ከተማ እና ቡራዩ ከተማ አሰልጣኝ የነበሩትን መኮንን ማሞን አሰልጣኝ አድርጎ መቅጠሩ ይታወሳል።
አሰልጣኙ ጅማ አባቡናን ከተረከቡ በኋላ ካደረጓቸው ሰባት ጨዋታዎች ውስጥ ሁለቱን አሸንፈው ሁለት አቻ ሲለያዩ በሶስቱ ሽንፈት ሽንፈት አስተናግደዋል። የተጠበቀውን ውጤት ባለማስመዝገባቸው ምክንያትም በተደጋጋሚ ከደጋፊዎች ተቃውሞ እያስተናገዱ የቆዩ ሲሆን ትናንት በዘጠነኛው ሳምንት ከነጌሌ ቦረና ጋር በሜዳቸው አቻ መውጣታቸውን ተከትሎ ከቡድኑ ጋር ዛሬ በስምምነት እንደተለያዩ ታውቋል።
አባ ቡና በቀጣይ ዋና አሰልጣኝ እስኪሾም ድረስ በምክትል አሰልጣኞች እየተመራ የሚቀጥል ይሆናል፡፡