ናይጄርያዊው አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢ ከጅማ አባጅፋር ጋር ያደረገው ቅድመ ስምምነት እክል እንደገጠመው ታውቋል።
የውል ዘመኑ ሳይጠናቀቅ በስምምነት ከግብፁ ኢስማይሊ ጋር የተለያየው ናይጄሪያዊው ኦኪኪ አፎላቢ በጥረ ወር የዝውውር መስኮት መከፈቱን ተከትሎ ወደ ቀድሞ ክለቡ ጅማ አባጅፋር ዳግም ተመልሶ ለመጫወት ከስምምነት መድረሱ ይታወቃል። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የሚገኘው ኦኪኪ አፎላቢ አስቀድሞ ከክለቡ ጋር ባደረጉት ስምምነት መሠረት ወደ ጅማ ያቀናል ተብሎ ቢጠበቅም ጅማ አባጅፋር በቅድመ ስምምነቱ መሰረት እፈፅማለው ያለውን ክፍያ ሊያሟላ ባለመቻሉ ውሉ ሊቋረጥ እንደሚችል ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
ጅማ አባጅፋር ቀድሞ የተስማማውን ውል የማይፈፅም ከሆነ በዚህ ሁለት ቀን ውስጥ ኦኪኪ አፎላቢ ወደ ሌሎች የፕሪምየር ሊግ ክለቦች ሊያመራ ይችላል ተብሏል። መቐለ 70 እንደርታ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና አዳማ ከተማም ከተጫዋቹ ጋር ስማቸው የተያያዙ ክለቦች ናቸው።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡