ማረፍያ ቤት የሚገኘው ራምኬል በኮንጎው ጨዋታ ላይሰለፍ ይችላል

የብሄራዊ ቡድኑ አጥቂ ራምኬል ሎክ በተከሰሰበት ወንጀል ምክንያት ለብሄራዊ ቡድን ጨዋታ ላይደርስ እንደሚችል ተሰምቷል፡፡

አምና ከሁለት ግለሰቦች ጋር በፈጠረው ግጭት ተከሶ እና ለጥቂት ቀናት ማረፍያ ቤት ቆይቶ የነበረው ራምኬል ሎክ የፍርድ ሂደቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ በማረፍያ ቤት እንዲቆይ ተወስኖበታል፡፡ ራምኬል በአሁኑ ወቅት የሚገኘው በየካ ክፍለከተማ ፖሊስ ጣቢያ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡

ብሄራዊ ቡድኑ ትላንት ባደረገው ልምምድ እና ዛሬ ለሁለት ተከፍሎ ባደረገው ጨዋታ ላይ ራምኬል ሎክ መካፈል አልቻልም፡፡

የራምኬል ጉዳይ በፍጥነት ከተጠናቀቀ እና በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት ውስጥ ውሳኔ ካገኘ አልያም የዋስ መብቱ ከተከበረለት ምናልባት ለቅዳሜው ጨዋታ ሊደርስ ይችላል፡፡

ያጋሩ