በተስተካካይነት ተይዘው ከነበሩ የ2ኛው ሳምንት ጨዋታዎች መካከል አንዱ የነበረው አዳማ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ 0-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
አዳማ ከተማ ከወላይታ ድቻ ጋር ነጥብ ከተጋራበት ጨዋታ ሱለይማን ሰሚድን እና ሙሉቀን ታሪኩን በኤፍሬም ዘካርያስ እና ከህመም በተመለሰው ዳዋ ሆቴሳ ተክቷል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ደግሞ ከፋሲል ከነማ ጋር አቻ ከተለያየው ቡድን ውስጥ ታደለ መንገሻ በአቡበከር ሳኒ የተቀየረበት ለውጥ ብቻ ነበር የተደረገው። ሆኖም ባልተጠበቀው ቅያሪ በማሟሟቅ ላይ ሳለ ጉዳት የገጠመው ምንተስኖት አዳነ በፍሬዘር ካሳ ተተክቷል።
መጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ በአዳማዎች ፈጣን ጥቃት ቢጀምርም መሀል ሜዳ ላይ የሚደረጉ ፍትጊያዎች የተበራከቱበት እና ቡድኖቹ በጣም በጥቂት አጋጣሚዎች ወደ ግብ የደረሱበት ነበር። በርግጥም ሁለቱም በድኖች የተጋጣሚያቸውን ጠንካራ ጎኖች በመቋቋሙ በኩል ተስካቶላቸው ነበር። እንደ ምንተስኖት ሁሉ አስቻለው ታመነንም በጉዳት ለማጣት ተቃርበው የነበሩት ጊዮርጊሶች በአማካዮቻቸው በተለይም በሙሉዓለም መስፍን አማካይነት የከንዓን ማርክነህን እንቅስቃሴ በቅርበት በመከታተል የአዳማ የኳስ ፍሰት ከመሀል ሜዳው ካለፈ በኋላ ፍሬ እንዳያፈራ አድርገዋል። አዳማዎችም የጊዮርጊሶችን ተሻጋሪ ኳሶች ወደ ግብ ክላቸው ከመላካቸው በፊት ጊዜን እና ክፍተትን በመንፈግ ከኳስ ውጪ እንደቡድን በመከላከሉ ጥሩ ነበሩ።
ቡድኖቹ የተሻለ ክፍተትን ለማግኘት የተጫዋቾች የሚና ለውጥ ሲያደርጉ ቢታይም ውጤቱ ግን እምብዛም ነበር። አዳማዎች በቀኝ አማካይነት የተሰለፈው ኤፍሬም ዘካርያስን ከበረከት ደስታ ጋር በመቀያሮየር እንዲሁም ረዘም ያሉ ኳሶችን ለዳዋ በመጣል የወሰዱት አማራጭ የጊዮርጊስን የኋላ ክፍል ማስጨነቅ አልቻለም። ጊዮርጊሶች ባልታሰበ መልኩ በአማካይነት ያስጀመሩት በኃይሉ አሰፋንን የመስመር ተመላላሽነት ሚና ከነበረው አቡበከር ሳኒ ጋር በመለወጥ ከፊት አጥቂዎቻቸው ጅርባ ከነበረው ቦታ ላይ በመነሳት ጫና ለመፍጠር ያደረጉት ጥረት ጥሩ ሲንቀሳቀስ የዋለው ኢስማኤል ሳንጋሬን አልፎ መግባት አልሆነላቸውም።
26ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር በተነሳ ኳስ በጊዮርጊስ ሳጥን አቅራቢያ ጥሩ ክፍተት አግኝተው የነበሩት አዳማዎች በከነዓን ፣ በረከት እና ዳዋ አማካይነት ግልፅ የማግባት ዕድል ለመፍጠር ቢቃረቡም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። በዚሁ ደቂቃ ላይ ተቃራኒው አቅጣጫ ሳላዲን ሰዒድ ከርቀት ያደረገው ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራ የመጀመሪያ የጨዋታው ሙከራ ሆኗል። ጊዮርጊሶች የተሻለ በሚባል የአጋማሹ ሙከራቸው 29ኛው ደቂቃ ላይ ሳላዲን ሙሉዓለም ከከነዓን ከቀማው ኳስ ወደ አዳማ ሳጥን ተጠግቶ አክርሮ የመታውን ኳስ ሮበርት አድኖበታል። በነዚህ ደቂቃዎች መጠነኛ መነቃቃት አሳይቶ የነበረው ጨዋታም ወደ ቀደመው የመሐል ሜዳ ፍትጊያ ተመልሶ ቡድኖቹ ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው እጅግ የተሻለ እና ሁለቱም ቡድኖች ግብ ለማስቆጠር ከጫፍ የደረሱበት ነበር። ቅዱስ ጊዮርጊሶች ወደ ግብ በመድረስ ቅድሚያውን ሲወስዱ 49ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ከሳላዲን ተቀብሎ ያደረገው ሙከራ ወደ ውጪ ወጥቷል። ነገር ግን በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ባለሜዳዎቸ አዳማዎች የሚሰነዝሯቸው ድንገተኛ ጥቃቶች ጎልተው መታየት ጀምረዋል። ወደ ግራ መስመር አድልቶ በመንቀሳቀስ ራሱን ነፃ ማድረግ የጀመረው ከንዓንም መሀል ላይ የሚቋረጡ ኳሶችን በመጠቀም በተሻለ መልኩ ተፅዕኖ ሲፈጥር ታይቷል። ተጫዋቹ 51ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻማ ኳስ ሲጨረፍ አግኝቶ ከሳጥን ውስጥ ያደረገው ሙከራም ለጥቂት ነበር በግቡ ቋሚ በኩል የወጣው። 56ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ከከነዓን በደረሰው ኳስ ከማታሲ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ያመከነው ኳስም አዳማዎች የፈጠሩት ሌላ ያለቀለት የግብ አጋጣሚ ነበር። ቡድኑ ከምንም በላይ መሪ ለመሆን የተቃረበው ግን 71ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ሆኖም በጊዮርጊስ ሳጥን ውስጥ ዳዋ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ ወደ ኋላ የመለሰውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ቴዎድሮስ ታፈሰ አክርሮ ቢሞክርም ኳስ በግቡ አግዳሚ የውስጥ ክፍል ተመልሳለች።
በነዚህ ሙከራዎች ጫና ውስጥ የገቡት ጊዮርጊሶች አሜ መሀመድን በማስገባት ፊት ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር ሲሞክሩ ጨዋታውን ከማረጋጋት ባለፈ በተሳካ ሁኔታ ወደ ማጥቃቱ የገቡት ታደለ መንገሻ ወደ ማዳ ከገባበት 77ኛ ደቂቃ በኋላ ነበር። አማካዩ በገባ በሁለት ደቂቃ ውስጥ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ በሮበርት ሲመለስ 82ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ሌላኛው ተቀያሪ አሜ ከሳላዲን በደረሰው ኳስ ከሮበርት ጋር ተገናኝቶ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል። እስከመጨረሻው ተጋግሎ የቀጠለው ጨዋታም በጭማሪ ደቂቃ ሌሎች ከባድ ሙከራዎችን አስተናግዷል። በተለይም ጊዮርጊሶች ማታሲ በፍጥነት ባስጀመረው እና ሳላዲን እና አሜ ይዘውት በገቡት ኳስ ጨዋታውን ለማሸነፍ ተቃርበው ነበር። ሆኖም ሳጥን ውስጥ አሜ ተከላካዮችን እና ሮበርትን አሸማቆ ወደ ግብ የላከው ኳስ በቴዎድሮስ ታፈስ ብቃት ከመስመር ላይ ሊድን ችሏል። በሰከንዶች ልዩነት ኢስማኤል ሳንጋሪ ከሳጥን ውጪ ከባድ ሙከራ አድርጎ ማታሲ ካዳነበት በኋላም ጨዋታው ፍፃሜውን አግኝቷል።
በውጤቱም ቅዱስ ጊዮርጊስ በተከታታይ ለሁለተኛ አዳማ ከተማ ደግሞ ለሦስተኛ ጊዜ ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት ተገደዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡