የአሰልጣኞች አስተያየት | ወላይታ ድቻ 1-2 ሲዳማ ቡና

በአዲስ አበባ ስታድየም አመሻሹ ላይ የተደረገው የወላይታ ድቻ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጠተዋል።

ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና 

ጨዋታው ጥሩ ነበር። በተለይ ከእረፍት በፊት ኳሱን ተቆጣጥረን ለመጫወት ችለናል። እነርሱ ለመከላከል ማሰባቸው ይህን ለማስከፈት ትንሽ ተቸግረን ነበር። ከእረፍት በኋላ ለተጫዋቾቻችን የነገርናቸውን በሚገባ አስተካክለው በመግባታቸው ጎል አስቆጥረን መጫወት ጀምረን ነበር። ሆኖም ቀይ ካርዱ ትንሽ ስሜታዊ አድርጎናል። ቀይ ካርዱ የተሰጠበት ምክንያት ምን እንደሆነ አናውቅም። ተጫዋቾቹ ሊሰዳደቡ ይችላሉ፤ ዳኛውም ለሁለቱም ቢጫ ካርድ ነበር ሊሰጡ የሚገባው። ለአንዱ ቀይ ለአንደኛው ቢጫ መሰጠቱ ለምን እንደሆነ አልገባኝም። ኳስ ይዘን እየተጫወትን ባለንበት ሰዓት ይህ ነገር መፈጠሩ በቡድኔም እንቅስቃሴ ላይ ተፅእኖ አድርጎ ተጫዋቾቼ ተረብሸዋል። ወደ መከላከሉ ስለመጣን በረጃጅም ኳሶች እየመጡ ያስቸግሩን ነበር። ፈጣሪ ይመስገን አሸንፈን ወተናል። 

ዘነበ ፍስሃ – ወላይታ ድቻ

ስለ ጨዋታው 

ጨዋታው ጥሩ ነበር። እንደጠበቅነው ውጤቱ ጥሩ ባይሆንም ጨዋታው ጥሩ ነው። ተጫዋቾቼ ጨዋታውን ለማሸነፍ የነበራቸው ፍላጎት ጥሩ ቢሆንም እንቅስቃሴያችን ጥሩ አልነበረም። የትኩረት ማነስ ይታይባቸው ነበር፤ ኳሶቻችን በጣም ይቋረጡ ነበር። በተለይ ያገኘናትን አንድ ግልፅ የጎል አጋጣሚ ብንጠቀም ኖሮ ጨዋታው ይቀየር ነበር። ይህ አለመሆኑ ዋጋ አስከፍሎናል።

በተከታታይ ጨዋታ ውጤት እየራቃቸው ስለመሆኑ 

እንግዲህ ሁልጊዜ ጎል የሚቆጠርብን ከትኩረት ማነስ እና ያገኘውን አጋጣሚ ያመጠቀም ክፍተቶቻችን ናቸው። ዛሬም የሆነው ይሄ ነው። ይሄን በስራ ለማስተካከል እየሰራን ነው። ግን ሊቀረፍ አልቻለም። ወደ ፊት ባለን ነገር አሻሽለን ጥሩ ውጤት ይዘን ለመውጣት ጠንክረን መስራት አለብን።

ጨዋታውን በሜዳቸው ያለማድረጋቸው ጉዳት

ይህ ለእኛ ትልቅ ጉዳት ነው። በሜዳችን ባለመጫወታችን የሜዳ ዕድላችንን አጥተናል። ይህ ደግሞ ለእኛ ጉዳት ነው። ያው ፌዴሬሽን የወሰነውን ውሳኔ እንቀበላለን እንጂ ወደን አይደለም እዚህ የመጣነው። በግዳጅ ነው፤ ሆኖም ውጤት በፀጋ እንቀበላለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *