የአሰልጣኞች አስተያየት | ደደቢት 0-3 መከላከያ

በትግራይ ስታድየም ደደቢት እና መከላከያ ካደረጉት ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች የሰጡትን አስተያየት እነሆ።
“ማሸነፋችን የበለጠ እንድንነሳሳ ይረዳናል” ሥዩም ከበደ

ስለጨዋታው 

ላለፈው አንድ ወር ከአዳማ ጨዋታ ጀምሮ ቡድናችን እየወረደ ነበር። ዛሬ ማሸነፍ ለኛ ጥሩ ነገር ነው፤ በአጠቃላይ የቡድናችን ስሜት ጥሩ አልነበረም። ወደ አሸናፊነት ካልመጣህ እንዚህ ነገሮች አስቸጋሪ ናቸው። 

ዛሬ በተለይም መጀመርያ አጋማሽ ላይ እንደ እቅዳችን ጫና አድርገን ያገኘናቸው ግቦች በጣም ጠቅመውናል። ከዕረፍት በኃላም እንደዛ ነበር፤ ሁለተኛው አጋማሽ የምንፈልገው ስላገኘን ብዙ መጫንም አስፈላጊ አይደለም ቀጣይ የሚጠብቁን ጠንካራ ጨዋታዎች አሉ። በአጠቃላይ ማሸነፋችን ግን የበለጠ እንድንነሳሳ ይረዳናል።

ስለ መቐለ የአንድ ሳምንት ቆይታቸው

ሰው ስፖርት ወዳድ ነው። ትግራይ ደስ ይላል፤ አቀባበሉ እና ሌላው ነገር ጥሩ ነው። ባለፈው ተሸንፈንም እንኳ እየወጣን የሰጡን ድጋፍ ደስ ይላል። በእንደዚ ዓይነት ደጋፊ መጫወት እጅግ ያረካል። በቆይታችን የተደረገልን ነገር ሁሉ እጅግ መልካም ነው። እንደውም ሌላ ጨዋታ ከወልዋሎ ጋርም ይቀረናል፤ እንደገና በፍቅር እንመለሳለን።

“በቀጣይ ከዚ በፊት የምናቀውን ደደቢት በታዳጊዎች ተክተን እንሰራለን” መለሰ ጋብር (ምክትል አሰልጣኝ)

እኛ ታዳጊ እንደመያዛችን መጠን የመርሃግብር መደራረቦች አሉ፤ ጫና የፈጠረብንም እሱ ነው። በሳምንቱ መጨረሻ ሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ ከባድ ጨዋታ አድርገን ነው የመጣነው። በጣም ጉልበት የሚጨርስ ጨዋታ ነበር። ከሱ ሳናገግም ነው ወደዚ ጨዋታ የቀረብነው። ውጤቱም እንዳያችሁት ነው። ወጣቶች እንደመሆናቸው መጠን በሂደት ይስተካከላል።

ስለ ቡድኑ ቀጣይ ጉዞ

ዓመቱ መጀመርያ ከብዶን እንደጀመርን ግልፅ ነው። ለክለቦች ምሳሌ እንሆናለን ብለን በታዳጊ ነው የጀመርነው። አንድ ነገር ስትጀምር ደሞ ፈተናዎች ይበዛሉ። በሂደት እያስተካከልን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ በታዳጊዎች አንድ ነገር እናሳያለን ብለን ነው የጀመርነው።

ስለ ወቅታዊው አስከፊ ውጤት

እየሰራን ያለነው እሱን ለማስተካከል ነው። ከስህተትህ እየተማርክ ነው የምትሄደው ለውጦችም ነበሩ። እያንዳንዱን ነገር አስተካክለን በቀጣይ ከዚ በፊት የምናቀውን ደደቢት በታዳጊዎች ተክተን እንሰራለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *