የመቐለ እና ፋሲል ተስተካካይ መርሐ ግብር ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።
ከ3ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል የነበረው የመቐለ እና ፋሲል ጨዋታ በትግራይ እና አማራ ክለቦች መካከል በነበረው ልዩነት ተላልፎ የቆየ ሲሆን ነገ ከ 09፡00 ጀምሮ በትግራይ ስታድየም ይከናወናል። ከላይ ካሉት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሲዳማ ቡና ጋር ያላቸው የነጥብ ልዩነት ወደ ሦስት ነጥብ ዝቅ ያለላቸው መቐለዎች ወደ ሊጉ መሪነት ለመምጣት ነገሮች ተመቻችቶላቸዋል። የነገን ጨምሮ ሦስት ተስተካካይ ጨዋታዎች ያላቸው መሆኑ አምስት ጨዋታዎችን በተከታታይ ከማሸነፋቸው ጋር ሲታይ የመጀመሪያውን ዙር በ1ኛነት የማጠናቀቅ ዕድላቸው ሰፍቷል። ስድስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ፋሲሎችም በተመሳሳይ መሪ የመሆን ዕድሉ አላቸው። በርግጥ ያለፉትን ሦስት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ማጠናቀቃቸው ወደ ኋላ ቢያስቀራቸውም ነገ ድል ከቀናቸው የተጋጣሚያቸውን የ3ኛነት ደረጃ በመረከብ በመሪዎቹ ላይ ጫና ማሳደራቸው አይቀርም። ጨዋታው በሂሳብ ስሌት በሰንጠረዡ አናት የመቀመጥ ዕድል ባላቸው ክለቦች መካከል መደረጉም ፉክክሩን ከፍ ያለ እንደሚያደርገው ይጠበቃል።
መቐለ 70 እንደርታ በመከላከያው ጨዋታ ጉዳት የገጠመው ሐይደር ሸረፋን ጨምሮ ሳሙኤል ሳሊሶ ፣ ፣ አቼምፖንግ አሞስ እና አሸናፊ ሃፍቱን በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ አይጠቀምም። በፋሲል በኩል ሙጂብ ቃሲም ፣ ዮሴፍ ዳሙዬ እና ወደ ልምምድ የተመለሰው ፋሲል አስማማው ለጨዋታው የማይደርሱ ሲሆን ሱራፌል ዳኛቸውም በቅጣት ወደ መቐለ አልተጎዘም፡፡ በጊዮርጊሱ ጨዋታ ተጎድቶ የወጣው አብዱርሀማን ሙባረክ ግን ወደ ሜዳ እንደሚመለስ ይጠበቃል።
ከአማኑኤል ገብረሚካኤል እና ያሬድ ከበደ ጥምረት ብዙ እያተረፈ የሚገኘው መቐለ 70 እንደርታ ነገም በሁለቱ አጥቂዎች የፊት መስመር እንቅስቃሴ ላይ ተመስርቶ በቀጥተኛ አጨዋወት በፋሲል ሳጥን ውስጥ ክፍተቶችን የመፈለግ ዕቅድ ሊኖረው ይችላል። በዚህ ውስጥ የመስመር አማካዮቹ የማጥቃት ተሳትፎ የጎላ ሲሆን የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ማግኘት ላይ ትኩረት ከሚያደርገው ተጋጣሚያቸው የአማካይ ክፍል ጥንካሬ አንፃርም ሲታይ የሐይደር አለመኖር እንዳለ ሆኖ የባለሜዳዎቹ የግብ አጋጣሚዎች ከሁለቱ መስመሮች የሚመነጩ ይመስላል። በፋሲል ከነማ በኩል በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ የነበረው ተመሳሳይ አቀራረብ እንደሚኖረው ይጠበቃል። አፄዎቹ በተለይም ግብ ካገኙ በኋላ እንደቡድን የመከላከል አቅማቸው መጎልበቱ ነገም ተጠቃሚ ሊያደርጋቸው የሚችል ሲሆን የማጥቃት ሽግግሩ ፍጥነት ዝግ ማለት ግን ከጠንካራው የመቐለ የኋላ ክፍል ውስጥ የመቀባበያ ክፍትቶችን ለማግኘት እንዳይቸገሩ ያሰጋቸዋል። በቅጣት የማይኖረው ሱራፌል ከአማካይ ክፍል በቀጥታ ለአጥቂዎቹ የሚያደርሳቸው ኳሶችን ማጣቱ ግን የፋሲል የማጥቃት ሂደትን እንዳያሳሳው ያሰጋል።
የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– የአምናው መቐለ ከተማ ወደ ሊጉ ባደገበት ዓመት ከፋሲል ከነማ ጋር የተደረጉት የሁለቱም ዙር ጨዋታዎች በገለልተኛው አዲስ አበባ ስታድየም ላይ የተደረጉት ሲሆን ሁለቱም ጨዋታዎች ያለግብ የተጠናቀቁ ነበሩ፡፡ በመሆኑም በዛሬው ጨዋታ ግብ ከተቆጠረበ ሊጉ የግንኙነት ታሪካቸው የመጀመሪያው ይሆናል፡፡
– መቐለ 70 እንደርታ በትግራይ ስታድየም ስድስት ጨዋታዎችን አድረጎ አምስቱን በድል ሲወጣ በአንድ ጨዋታ ነጥብ ተጋርቷል፡፡
– ፋሲል ከነማ ከጎንደር ውጪ ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ሁለት ድል አስመዝግቦ ሦስት ጊዜ ነጥብ ሲጋራ አንድ ሽንፈት ገጥሞታል።
ዳኛ
– ከ13ኛው ሳምንት በኋላ ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ ይህን ጨዋታ ይመራል። አርቢትሩ ሁለቱን ቡድኖች አንድ አንድ ጊዜ የዳኘ ሲሆን እስካሁን በመራባቸው አራት ጨዋታዎች አስራ ሁለት የቢጫ ካርዶችን ሲሰጥ አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔም አሳልፏል።
ግምታዊ አሰላለፍ
መቐለ 70 እንደርታ (4-4-2)
ፍሊፔ ኦቮኖ
ስዩም ተስፋዬ – አሌክስ ተሰማ – አሚኑ ነስሩ – አንተነህ ገብረክርስቶስ
ያሬድ ብርሀኑ – ጋብርኤል አህመድ – ሚካኤል ደስታ – ዮናስ ገረመው
አማኑኤል ገብረሚካኤል – ያሬድ ከበደ
ፋሲል ከነማ (4-3-3)
ሚኬል ሳማኬ
ሰዒድ ሁሴን – ያሬድ ባየህ – ከድር ኩሊባሊ – አምሳሉ ጥላሁን
ኤፍሬም ዓለሙ – ሐብታሙ ተከስተ – በዛብህ መለዮ
አብዱርሀማን ሙባረክ – ኤዲ ቤንጃሚን – ሽመክት ጉግሳ
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡