ደደቢት የቀድሞ አስልጣኙን በድጋሚ ቀጠረ

በውጤት ማጣት ምክንያት አስልጣኞቹን ያሰናበተው ደደቢት ዳንኤል ፀሐዬን ወደ ቀድሞ ቤቱ መልሷል።

ባለፈው ማክሰኞ አሰልጣኞቻቸው አሰናብተው ሁለቱ ጨዋታዎች በግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ ይድነቃቸው ዓለሙ እየተመሩ ሁለት ጨዋታ ያደረጉት ሰማያዊዎቹ ባለፈው ሳምንት በቃል ደረጃ ከተስማሙት አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ ጋር የስድስት ወራት ውል ተፈራርመዋል። ባለፈው ሳምንት ለሁለት ዓመት ከስድስት ወር ከቆየበት ስሑል ሽረ ጋር በስምምነት የተለያዩት ዳንኤል ፀሐየ ትላንት ከመከላከያ ጋር በነበረው ጨዋታ በትግራይ ስቴድየም ተገኝተው ጨዋታውን የተከታተሉ ሲሆን ከዛሬ ጀምሮ ስራቸውን ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ ከዚ ቀደም በደደቢት ከታዳጊ ቡድን ጀምሮ የዋናው ቡድን ረዳት አሰልጣኝ ሆነው የሰሩ ሲሆን ለጥቂት ጊዜያትም በጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝነት ሰርተዋል። በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የአሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ረዳት አሰልጣኝ ሆነው ያሳለፉት የቀድሞ የጉና ንግድ ተጫዋች ያለፉት ዓመታት ደሞ ስሑል ሽረን በዋና አሰልጣኝነት በመምራት በአጭር ጊዜ የከፍተኛ ሊግ ቆይታ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማሳደጋቸው ይታወሳል።

አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ ከሹመቱ በኋላ በተለይ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ቡድኑን ለማትረፍ የሚቻላቸው እንደሚያደርጉ ገልፀዋል። “ቡድኑን ለማጠናከር እንሞክራለን። በርግጥ ፈተናዎች አሉ፤ ከሌሎች ክለቦች ብዙ ልዩነት አለ። በተጨማሪም ቡድኑ ታዳጊዎችን ነው የያዘው። ክለቡ ካለው አላማ ጋር ባለው ነገር ላይ የተወሰኑ ተጫዋቾችን ጨምሬ ለማሻሻል ነው አላማዬ፡፡ በተቻለኝ መጠነኝ ከወራጅ ቀጠናው ለማትረፍ በሚቻልበት ሁሉ መስራት እፈልጋለሁ። ምክንያቱም የተወሰነ ጨዋታዎችን አሸንፈህ ልትተርፍ ትችላለህ። ካላሸንፍክ ግን የነጥብ ልዩነቱ በጣም ሩቅ ነው፡፡” ብለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *