ከፊፋ በተገኘ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበት በተገዛው ህንፃ ዙርያ እስካሁን በይፋ የግዢውን አፈፃፀም እና ዝርዝር ሁኔታዎችን አስመልክቶ ፌዴሬሽኑ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት አለመቻሉ ጥያቄ አስነስቷል።
ከሁለት ዓመት በፊት በአቶ ጁነይዲ ባሻ የአስተዳደር ዘመን ፌዴሬሽኑ በተለያዩ ቦታዎች ተበታትኖ የሚሰጠውን አገልግሎት ወደ አንድ ለማምጣት በማሰብ የራሱ ህንፃ እንዲኖረው ፊፋን የገንዘብ እርዳታ መጠየቁ ይታወቃል። የእግርኳሱ የበላይ አካል ፊፋ የፌዴሬሽኑን ጥያቄ ተቀብሎ ከአንድ ዓመት በፊት ለህንፃው ግዢ ማስፈፀሚያ የሚሆን የ3 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርጓል።
በአቶ ጁነይዲ የስልጣን ዘመን በሪፖርተር ጋዜጣ በወጣ የጨረታ ማስታወቂያ መሰረት የህንፃው ግዢ ይፈፀማል ተብሎ ቢጠበቅም የስልጣን ጊዜያቸው በመጠናቀቁ ምክንያት የህንፃው ግዢ ሳይፈፀም የቆየ ሲሆን በአቶ ኢሳይያስ ጂራ የሚመራው ፌዴሬሽን የህንፃውን ግዢ መጠናቀቁ ተሰምቷል።
በአዲስ ዘመን እና በሪፖርተር ጋዜጣ በወጣ የጨረታ ማስታወቂያ መሰረት ቦሌ በወሎ ሰፈር አድርጎ ወደ ጎተራ ቄራ በሚወስደው መንገድ ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፅህፈት ቤት ጎን ባለ አምስት ፎቅ ዘመናዊ ህንፃ ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበት ግዢ እንደተፈፀመ እና በቀብድ ማያዣነት ለጊዜው 13 ሚሊዮን ብር ከፌዴሬሽኑ ካዝና በማውጣት ክፍያ መፈፀሙን ለማወቅ ችለናል። ምንም እንኳን እስካሁን ከፌዴሬሽኑ በኩል በይፋ የተሰጠ ማረጋገጫ ባይኖርም።
በህንፃው ግዢ ላይ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ፣ የቀድሞ ጊዜያዊ ዋና ፀሀፊ አቶ ሰለሞን ገብረሥላሴ እና የፋይናስ ክፍሉ ኋላፊ አቶ ነብዩ እንዲሁም ከህዝብ ግኑኝነት አንድ የቪዲዮ ካሜራ ባለሙያ ሲገኝ ለጊዜው ስማቸውን ያላወቅነው ሻጭ ባሉበት ተፈፅሟል። በቅርብ ጊዜ ውስጥ ዝርዝር ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣል ቢባልም እስካሁን ምንም ነገር የለም። ይህን ተከትሎ የተለያዩ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ።
አንደኛ በህንፃ ግዢ ዙርያ ፌዴሬሽኑ በይፋ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቆ ባለበት ሁኔታ ከላይ በተሰጠ ትዕዛዝ ጋዜጣዊው መግለጫው እንዲዘገይ ሆኗል የሚል ሲሆን ሁለተኛው ፌዴሬሽኑ ይህን ትልቅ ስራ ለምን በግልፅ ለሚዲያው ይፋ ማድረግ ያልተፈለገበት ምክንያት ምን ይሆን? በሻጭ እና በገዢ መካከከል ያለው ጉዳይስ ምንድነው? ሦስተኛው ደግሞ በህንፃው ግዢ ላይ መገኘት የሚገባቸው የፌዴሬሽኑ የቢሮ ኃላፊዎች ለምን አልተገኙም? የሚሉ ጥያቄዎች አስነስቷል።
ሶከር ኢትዮጵያ እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ የህንፃው ግዢ አፈፃፀም ላይ የአሰራርር ክፍተት በመኖሩ ምክንያት ውሉ ሊቋረጥ እንደሚችል እየተነገረ ይገኛል። ይህን ጥያቄ እና ሌሎች ጉዳዮችን ይዘን ለፌዴሬሽኑ ህዝብ ግኑኝነት ወ/ሮ ሠላማዊት ፈቅይበሉ ላቀረብነው ጥያቄ የተሰጠን ምላሽም ” መረጃ ለመሰጠት እስካሁን ይህ ነው ተብሎ የተጠናቀቀ ምንም ነገር የለም። ጉዳዩ በሂደት ላይ በመሆኑ መረጃ ለመስጠት እንቸገራለን። ሂደቱ ሲጠናቀቅ መረጃ የምንሰጥ ይሆናል።” ብላለች።
ከፌዴሬሽኑ ወደ ፊት የሚሰጠውን መረጃ እየጠበቅን በእኛ በኩል በህንፃው ግዢ ዙርያ ያሉንን መረጃዎች በቀጣይ ይዘን የምንቀርብ ይሆናል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡